“ጽዱና ውብ፤ ዘመናዊ የፍሳሽ እና የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን መዘርጋት ለነገ የማይባል ሥራ ነው” የደሴ ከተማ አሥተዳደር

32

ደሴ፡ ግንቦት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደሴ ከተማ አሥተዳደር ብክለትን ለመቀነስ እና ለማስወገድ “ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ” በሚል መሪ መልዕክት የተዘጋጀ የንቅናቄ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ “ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ” የስድስት ወራት የአካባቢ ጥበቃ የንቅናቄ ዘመቻ ማስጀመሪያ ጹሑፍ ቀርቦ ምክክር ተደርጎበታል።

የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ውብ ጽዱና ተስማሚ ደሴን በመፍጠሩ ሂደት የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ሚናው ከፍተኛ መኾኑ በምክክር መድረኩ ተመላክቷል።

የመድረኩ ተሳታፊ የከተማዋ ነዋሪዎች በሁለንተናዊ ለውጥ ውስጥ የምትገኘውን ከተማ ጽዱና ውብ ለማድረግ የንቅናቄ መድረክ መዘጋጀቱ አስፈላጊ ነው ብለዋል። ማኅበረሰቡ ተሳታፊ ያልኾነበት የጽዳት እና ውበት ሥራ ውጤታማ ሊኾን እንደማይችልም ተናግረዋል፡፡ ከከተማ አሥተዳደሩ ጎን በመኾን የከተማዋን ጽዳት እንደሚጠብቁም ነው ያስገነዘቡት።

የከተማ አሥተዳደሩ አካባቢ ጥበቃ ጽዳት እና ውበት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዬናስ ሰይድ የአካባቢ ብክለት በይደር የሚተው ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡ ኀላፊው ችግሩ ጊዜ በተሰጠው ቁጥር አሳሳቢነቱ እና አደገኛነቱ እየተባባሰ የሚመጣ በመኾኑ ፈጣን እና ወቅቱን የዋጀ መፍትሄ መስጠት ያሻል ነው ያሉት።

የከተማ አሥተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ሽመልስ ጌታቸው በደሴ ከተማ በሰላም፣ በመልካም አሥተዳደር እና በመሠረተ ልማት ዘርፍ የታየውን ውጤታማ ሥራ በጽዳት እና ውበት ዘርፍ ለመድገም በትኩረት ሥራ መጀመሩን ነው ለአሚኮ የገለጹት።

በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ “ጽዳት የዘመናዊ አስተሳሰብ ውጤት ነው” ብለዋል። “በከፍተኛ ጥግግት ውስጥ ኑሮውን ለሚገፋው የከተማችን ነዋሪ ጽዱና ውብ፤ ዘመናዊ የፍሳሽና የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን መዘርጋት ለነገ የማይባል ሥራ ነው” ብለዋል፡፡

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል የደሴ ከተማን በሆቴል እና በቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ ውብና ጽዱ ደሴን መፍጠር የከተማዋ ማኅበረሰብ ቀዳሚ ተግባር መኾን አለበት ነው ያሉት።

የአካባቢ ብክለትን ለማስወገድ እና የአስተሳሰብ ተነሳሽነትን ለመፍጠር ዓላማ አድርጎ የተፈጠረው የንቅናቄ መድረክ በተለያዩ መርሐ ግብሮች እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም የሚቀጥልም ይኾናል።

ዘጋቢ፡- ጀማል ይማም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደርን ጎበኙ፡፡
Next article“ስለ ኢትዮጵያ ተፋቀሩ፣ በአንድነትም ኑሩ”