“ዓላማችን ባሕር ዳር ከተማን የመማሪያ ማዕከል ማድረግ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

24

ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በዛሬው ዕለት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተገኙበት የከተማዋን የመንገድ ዳር ልማት የመጨረሻ ንድፍ እያስተዋወቀ ነው።

ከተማ አሥተዳደሩ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ንድፍ ርእሰ መሥተዳድሩን ጨምሮ የክልል እና የከተማ አሥተዳደሩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ነው እየተዋወቀ ያለው።

በከተማዋ የመንገድ ዳር ልማት የንድፍ ትውውቅ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በባሕር ዳር ከተማ የሚጀመረው የመንገድ ዳር ልማት ብዙ የማይጠይቅ፣ በተፈጥሮ የታደለ እና ምቹ ከባቢ ነው ብለዋል።

በክልሉ ዋና ዋና ከተሞች የመንገድ ዳር ልማቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያወሱት ርእሰ መሥተዳድሩ “ዓላማችን ባሕር ዳር ከተማን የመማሪያ ማዕከል ማድረግ ነው” ብለዋል። የከተማዋ መሪዎች ከሀገሪቷ መዲና የሥራ ተሞክሮ በመውሰድ ቀን ከሌሊት እንዲሠሩም የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።

የመንገድ ዳር ልማቱን በአጭር ጊዜ ውጤታማ ለማድረግ እንዲቻል የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ባለሙያዎቹን ልምድ እንዲያጋሩ መላኩን ያወሱት ርእሰ መሥተዳድሩ ለአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደርም ምሥጋና አቅርበዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ልምድን የማጋራት ድጋፍ አብሮ እና ተቀራርቦ ለመሥራት ያለንን ቁርጠኛ መሻት ያመላከተም ነበር ብለዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ባሕር ዳር በጣና ሐይቅ እና በዓባይ ወንዝ መካከል የበቀለች ውብ ከተማ ናት ብለዋል። የመንገድ ዳር ልማት ንድፉ ከታላቁ የዓባይ ወንዝ ድልድይ ግንባታ ምረቃት በኋላ የመጣ ተጨማሪ ውበት ስለመኾኑም ተናግረዋል።

ባሕር ዳር ከተማን ትንሽ ብናለማት ተፈጥሯዊ ውበቷ በቀላሉ መገለጥ የምትችል ከተማ ናት ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በጋራ፣ በትብብር እና በመናበብ ሠርተን የቱሪስት ማዕከል የኾነች ከተማን እንፈጥራለን ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየልማት እና የሰላም ማረጋገጥ ሥራው በትኩረት እየተሠራ እንደኾነ የሰሜን ሸዋ ዞን ገለጸ፡፡
Next articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደርን ጎበኙ፡፡