
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ ከሚገኙ የቱሪስት መስህቦች መካከል አናቤ የተፈጥሮ ጥብቅ ደን አንዱ ነው። 027 ገደሮ በተሰኘ ቀበሌ ውስጥም ይገኛል።
ከወረዳው ዋና ከተማ ከኮምቦልቻ በስተምሥራቅ 69 ኪሎ ሜትር የአስፋልት እና ጠጠር መንገድ እንዲሁም ከ30 ደቂቃ የእግር ጉዞ በኋላ ይደረሳል።
ደኑ 85 ሄክታር ስፋት ያለው እና በብዛት በዝግባ እንዲሁም በጽድ፣ ወይራ፣ መካኒሳ፣ ብሳና እና ዋንዛ የተሸፈነ ነው።
የአየር ንብረቱ ወይና ደጋ ሲኾን የመሬት አቀማመጡም ሸለቋማ እና ገደላማ ነው። የምንጮች እና ወንዞች ባለቤትም ነው። በውስጡም ሶረኔ ቆቅን ጨምሮ ድኩላ፣ ጦጣ፣ ዝንጀሮ፣ ቀበሮ፣ ጅብ፣ጉሬዛ፣ አቦሸማኔ እና ነብር ይገኙበታል።
ሥፍራው ከደርግ ሥርዓተ መንግሥት ጀምሮ እንደሚጠበቅ ይነገራል። አሁን ላይ ሁለት ጠባቂዎች ያሉት ሲኾን የቀበሌው ሕዝብም እንዲንከባከበው በየጊዜው ውይይት ይደረጋል። የጥብቅ ደኅንነት ደብተርም ወጥቶለታል።
በአካባቢው ማኅበረሰብ የዛፎች አባት ተብሎ የሚጠራ ግዙፍ የዝግባ ዛፍ በደኑ ምሥራቃዊ ስፍራ ይገኛል። ይህ ዛፍ ስዊድን ሀገር ከሚገኘው በውፍረቱ በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ከሰፈረው ዛፍ እንደሚበልጥ ይነገርለታል። በአንድ ወቅት ከስዊድን ሀገር የመጡ አጥኚዎች ይህ ዛፍ ከስዊድኑ ዛፍ ይበልጣል ማለታቸው ይነገራል። የወረዳው ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ባለሙያ አወል መሐመድ አደም የዛፉ ዙሪያ ውፍረት 13 ሜትር መድረሱን ገልጸዋል።
ጥብቅ ደኑ ሙሉ በሙሉ ስላልተጠና መሰል መጠን ያላቸው ዛፎች መኖር አለመኖራቸው ግን አይታወቅም።
ቀደም ሲል እስከ ደኑ የሚያደርስ የመኪና መንገድ ስለነበረው በርካታ ሰው ይጎበኘው እንደነበር ይነገራል። አሁን ላይም ተማሪዎች በሀገርክን እወቅ ፕሮግራም እና ምሁራን ለጥናት ሥራ ይጎበኙታል።
ለጥብቅ ደኑ መሰረተ ልማት ከተሟላለት እና ዛፉን በዓለም ሪከርድነት ማስመዝገብ ከተቻለ የቱሪስት ፍሰቱ ከፍተኛ እንደሚኾን እና ለማኅበረሰቡም ለሀገርም ጠቀሜታ እንደሚኖረው ይታሰባል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
