በምርት አሠባሠብ ላይ ብክነትን ለመቀነስ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

45

ባሕር ዳር: ግንቦት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እና የደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በመቅደላ ወረዳ በኩታ ገጠም የለማ የበጋ መስኖ ስንዴን ጎብኝተዋል፡፡ በወረዳው የጠቢ መስኖ ልማት ከ600 ሄክታር በላይ በኩታ ገጠም የለማ ሲኾን ከ800 በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡

በአማራ ክልል በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) 250 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ በክልሉ በተፈጠረ የፀጥታ ችግር ምክንያት 153 ሺህ ሄክታር ማልማት እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡በመቅደላ ወረዳ የተመለከቱት የበጋ መስኖ ስንዴ በጥሩ ቁመና ላይ እንዳለም ጠቁመዋል፡፡ የትምህርት ቤት መሬትን ለሥራ ፈላጊ ወጣቶች ብቻ አጫርተው የሥራ እድል እንዲፈጠርላቸው መደረጉ ትምህርት የሚወሰድበት ስለመኾኑም አመላክተዋል፡፡

በምርት አሠባሠብ ሂደት የምርት ብክነትን ለመቀነስ እንዲያስችልም በዚህ ዓመት 13 ኮምባይነሮችን በብድር ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱን አመልክተዋል፡፡ በቀጣይም በስፋት ትኩረት ተደርጎ ይሠራል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በሰው ኀይል ሲሠበሠብም ብክነትን በቀነሰ መንገድ መኾን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን በመስኖ ስንዴ ልማት የተስተዋሉ ጥንካሬዎች እና ጎደሎዎች ተለይቶ በክልሉ አስተያየት እንዲሰጥበት እና የጠቢ መስኖ ግድብ በመድረቁ አደጋ ውስጥ በመኾኑ ክልሉ የሚችለውን ድጋፍ አድርጎ ልማቱ እንዲቀጥል በማሰብ ጭምር የተዘጋጀ ጉብኝት መኾኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህ ዓመት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በተሻለ ሁኔታ ማልማት እንደተቻለ የጠቆሙት ዋና አሥተዳዳሪው ጽንፈኛ ኀይሉ የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ ጥረት ቢያደርግም የወሎ ሕዝብ ሰላም ወዳድ እና በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር በመኾኑ ለሰላም ዘብ በመቆሙ በተፈጠረ አንጻራዊ ሰላም የተገኘ ውጤት መኾኑን አብራርተዋል፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የአካባቢ የፀጥታ ኀይሎች ባደረጉት ጥረት እና ተጋድሎ የተገኘ አንጻራዊ ሰላም መኾኑንም አብራርተዋል፡፡ የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አህመድ ጋሎ በ2016 ዓ.ም በመስኖ እና በበልግ ከ35 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ለማልማት ታቅዶ 26 ሺህ 600 ሄክታር ማልማት ተችሏል፡፡ በዚህም 716 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት መታሰቡንም አስረድተዋል፡፡

በሄክታር 33 ኩንታል ስንዴ ለማምረት የታሰበ ቢኾንም አንዳንድ ወረዳዎች እስከ 42 ኩንታል ያመረቱበት ሁኔታ መፈጠሩንም ገልጸዋል፡፡ የጠቢ መስኖ ልማትም ቁመናው ሲታይ ምርታማነቱ ከዚህ የበለጠ እንደሚኾን ይገመታል ያሉት አቶ አህመድ በአጠቃላይ ምርትም ከተቀመጠው ግብ የበለጠ ሊገኝ እንደሚችል አመላክተዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው በዘንድሮ የበልግ ምርት 104 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ 103 ሺህ ለምቷል፡፡ ሰብሉም በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በኢትዮ-ቴሌኮም የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ አገልግሎትን ጎበኙ።
Next articleየተደበቀው ሃብት!