ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በኢትዮ-ቴሌኮም የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ አገልግሎትን ጎበኙ።

28

ባሕር ዳር: ግንቦት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በኢትዮ-ቴሌኮም የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ አገልግሎትን ጎብኝተዋል። የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢትዮ-ቴሌኮም የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተመስገን ጥሩነህ የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ የደረሰበትን ደረጃ አራዳ ጊዮርጊስ በሚገኘው የኢትዮ-ቴሌኮም የአገልግሎት መስጫ ማዕከል ተገኝተው ጎብኝተዋል።

ኢትዮ-ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየተካሄደ የሚገኘውን የነዋሪዎችን የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ አዲስ አበባን ጨምሮ በ29 ከተሞች በሚገኙ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላቱ በቅርቡ ማስጀመሩ ይታወቃል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ እስከ 2018 ዓ.ም መጨረሻ ለ90 ሚሊዮን ዜጎች ዲጂታል መታወቂያን ለማዳረስ ታቅዷል።

ከዚህም ውስጥ ኢትዮ-ቴሌኮም በወር በአማካይ 1 ሚሊዮን ዜጎችን በመመዝገብ ለ32 ሚሊዮን ዜጎች ተደራሽ በማድረግ ሀገራዊ ዕቅዱን 36 በመቶ እንደሚያከናውን ገልጿል። የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን ዕውን ለማድረግ ከሚያስፈልጉ አስቻይ ሥርዓቶች ውስጥ አንዱ ሲሆን ለአካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በክልሉ የተጀመረውን ልማት ከዳር በማድረስ ተጠቃሚ ለመኾን ሕዝቡ የአካባቢውን ሰላም ማፅናት እና አንድነቱን ማጠናክር ይገባዋል” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ
Next articleበምርት አሠባሠብ ላይ ብክነትን ለመቀነስ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡