
ደሴ: ግንቦት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በደቡብ ወሎ ዞን አርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኝ ተከላ አካሂዷል። በልዩ ወረዳው የተተከሉት ፍራፍሬዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው በመኾኑ የአካባቢው አርሶ አደሮች በባለቤትነት ሊንከባከቧቸው እንደሚገባም ተገልጿል።
በ24 ተፋሰሶች ከ800 ሄክታር በላይ መሬት እየለማ መኾኑን የገለጹት የአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አደም እንድሪስ እየተሠሩ ያሉ የጠረጴዛ እርከን ሥራዎች የአካባቢውን ሥነ ምኅዳር ከመጠበቅ አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተናግረዋል። የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አሕመድ ጋሎ በዞኑ ከ2016 የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ቀደም ብሎ በተለያዩ አካባቢዎች የበጋ የፍራፍሬ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እየተከናወነ ነው ብለዋል።
እስካሁ ከ29 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ መከናወኑን የገለጹት አቶ አሕመድ በቀጣይ የክረምት ወቅት ከ78 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በአረንጓዴ አሻራ ላይ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ጠቁመዋል። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር.) “በአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ እየተሠራ ያለው የግብርና ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት” ብለዋል። ክልሉ ለወረዳው የውኃ መሳቢያ ፓምፖችን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም በመርሐ ግብሩ ላይ ገልጸዋል።
በክልሉ እየተሠሩ ያሉ የአትክልት እና የፍራፍሬ ሥራዎች ለክልሉ የኢኮኖሚ ምንጭ በመኾናቸው በቀጣይ በትኩረት እንደሚሠራ ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል። የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ በክልሉ የተጀመረውን ልማት ከዳር በማድረስ ተጠቃሚ ለመኾን ሕዝቡ የአካባቢውን ሰላም ማፅናት እና አንድነቱን ማጠናክር ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ሰልሀዲን ሰይድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
