“በመጪው ክረምት አሲዳማ መሬቶችን በማከም ከፍተኛ ምርት ለማምረት እየተሠራ ነው” ግብርና ቢሮ

41

ደሴ: ግንቦት 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ለግብርና መሪዎች እና ባለሙያዎች የአሲዳማ አፈር ልማት የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የ2016/17 የምርት ዘመን የአሲዳማ አፈር ልማት ዕቅድ የንቅናቄ መድረክ በደሴ ከተማ አካሂዷል፡፡ በክልሉ ከሚታረሰው መሬት 1 ነጥብ 4 ሚልዮን ሄክታር መሬት በጠንካራ አሲድ መጠቃቱን እና 28 ሚልዮን ሄክታር መሬት ደግሞ በመካከለኛ አሲዳማነት መጠቃቱን በንቅናቄ መድረኩ ሪፖርት ቀርቧል፡፡

የተሻለ ዝናብ በሚያገኙ በምዕራብ አማራ ዞኖች ማለትም በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ በምሥራቅ ጎጃም፣ በምዕራብ ጎጃም፣ በሰሜን ጎጃም፣ በማዕከላዊ ጎንደር፣ በሰሜን ጎንደር እና በደቡብ ጎንደር ዞኖች ስርጭቱ ከፍተኛ ሲኾን በምሥራቅ አማራ ዞኖች ማለትም በሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ወሎ እና ሰሜን ሸዋ የአፈር አሲዳማነት ስርጭቱ እየተስፋፋ መምጣቱ ተገልጻል፡፡

የተዛባ የእርሻ አስተራረስ እና አጠቃቀም፣ የአፈር ንጥረ ነገሮች በከፍተኛ የዝናብ ጎርፍ መታጠብ እና የአፈር መሸርሸር ለአሲዳማ አፈር መፈጠር በመንስኤነት የተጠቀሱ ችግሮች ናቸው፡፡ የመድረኩ ተሳታፊ የዘርፉ ባለሙያዎች ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር አሲዳማ አፈርን በኖራ ማከም ለነገ የማይባል ሥራ በመኾኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው በመጪው ክረምት የግብርና ሥራዎች ከፍተኛ ምርት ለማምረት እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። እንደ ክልል ያለውን መሬት ወደ ሥራ በማስገባት 5 ነጥብ 18 ሚልዮን ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 169 ሚልዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት በዕቅድ እየተሠራ እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት፡፡

የ2016/17 የምርት ዘመን ከፌዴራል ጀምሮ በተሰጠው ትኩረት መሠረት በ10 ዞኖች እና 87 ወረዳዎች 20 ሺህ 785 ሄክታር መሬት ላይ 623 ሺህ 550 ኩንታል ኖራ በመጠቀም እና ሰፋፊ ሠርቶ ማሳያዎችን በማካሄድ በአሲዳማ አፈር የተጠቁ አካባቢዎችን ለማከም ዕቅድ መያዙም በመድረኩ ተነስቷል፡፡

ዘጋቢ፦ ፊኒክስ ሀየሎም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው” የከተማዋ ነዋሪዎች
Next articleየፈተና ጥሪ ማስታወቂያ!