
ሰቆጣ: ግንቦት 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል በተከሰተው የሰላም እጦት ምክንያት በክልሉ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ተፅዕኖ አሳድሯል። ይህንን ችግር ለመፍታትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ያቀረቡት የሰላም ጥሪ ወቅቱን የጠበቀ እና አግባብነት ያለው መኾኑን በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የሰቆጣ ከተማ ነዋሪው አቶ አሰፋ ፀሐዩ ከጦርነት ውድመት እና ሞት ነው የሚገኘው፤ ከሰላም ግን እድገት እና አንድነት ይገኛል ብለዋል። ለአማራ ክልል የሚቆረቆሩ አካላት በሰላማዊ መንገድ ልዩነቶችን ሊፈቱ እንደሚገባም አሳስበዋል። ሌላዋ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ፍሬ ደሳለኝ መንግሥት አባት ነው፤ አንድ አባት ደግሞ ልጁ ቢያጠፋ ይቅር ይለዋልና አሁንም መንግሥት ያቀረበው የሰላም ጥሪ የሚጠበቅ ነው ብለዋል።
ካለፉት ጊዜያቶች ትምህርት መውሰድ ይገባል ያሉት የሰቆጣ ከተማ ነዋሪው ኮማንደር ነጋሽ ተንሳይ በዋግ ኽምራ ያሉ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ በመፈታታቸው አካባቢው ሰላም እንደኾነ ገልጸዋል። በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ያለውን የሰላም እጦት ለመፍታትም የውስጥ አንድነትን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
