
ባሕር ዳር: ግንቦት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ከሚያነሷቸው ቀዳሚ ጥያቄዎች መካከል የንጹሕ መጠጥ ውኃ አንደኛው ነው፡፡ የከተማዋን የሕዝብ ብዛት፣ ፍላጎት እና የሥራ እንቅስቃሴ የሚመጥን የውኃ አቅርቦት የለምና ነዋሪዎች ሲጠይቁ ኖረዋል፤ ዛሬም ጥያቄ ላይ ናቸው፡፡ በየቤታቸው የሳቧቸው የውኃ ቧንቧዎች በሳምንታት ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ነው ውኃ የሚያፈስሱት፡፡
እንግዳ ለማይጠፋባት ታሪካዊ ከተማ የውኃ ችግር ለኑሮ አስቸጋሪ ኾኗል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የጎንደር ከተማ ነዋሪዎችን የውኃ ችግር ሊፈታ ይችላል የተባለለት መመሪያ ከሰሞኑ ሰጥተዋል፡፡ ይሄም መመሪያ የከተማዋን የውኃ ችግር በፍጥነት እና በዘላቂነት ይፈታ ይኾን የሚል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
የጎንደር ከተማ ነዋሪው አቶ ዳንኤል ከበደ የጎንደር ሕዝብ የውኃ ጀሪካን እየያዘ እየተንከራተተ፣ በውኃ ጥም ሲቸገር የአንገረብ ግድብ በደርግ ዘመነ መንግሥት ተሠራ ይላሉ፡፡ በ1976 ዓ.ም ግድቡ እንደተገደበ የነገሩን አቶ ዳንኤል እስከ 1995 ዓ.ም ገደማ ድረስ በጎንደር ከተማ የውኃ ችግር አልነበረም ማለት ይቻላል፤ ከዚያ በኃላ ግን ሕዝቡ እየበዛ በመሄዱ የውኃ አቅቦት እና የሕዝብ ፍላጎት አልገናኝ አለ ነው የሚሉት፡፡
ይባስ ብሎ የአንገረብ ግድብ በደለል እየተሞላ ሄደ፤ በደለል ሲሞላም የሚሰጠው ውኃ እየቀነሰ ሄደ፡፡ ውኃው ይቀንሳል፤ የከተማዋ ሕዝብ ይጨምራል፤ በዚህ መካከል የጎንደር ከተማ በውኃ ተጠማች ነው ያሉት፡፡ ለከተማዋ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ለማቅረብ የመገጭ ግድብ ተጀመረ፣ ከዚያ ባለፈም ጥልቅ ጉድጓዶች መቆፈር ተጀመረ፤ ነገር ግን የሚጠበቅባቸውን ውኃ ሳይሰጡ ቀሩ፡፡ ከቆላድባ የተቆፈሩ የውኃ ጉድጓዶች ለአዘዞ አካባቢ አገልግሎት መስጠታቸውንም አንስተዋል፡፡
“የጎንደር ከተማ ሕዝብ ውኃ ተጠምቷል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት መመሪያ ችግራችንን እንደሚፈታ እንጠብቃለን” ሲሉም ተናግረዋል። ከአሥራ አምስት ቀናት በታች ውኃ ማግኘት የሚታሰብ አይደለም፤ በውኃ ችግር ምክንያት ጎንደር ላይ አገልግሎት ለመስጠትም አስቸጋሪ እንደኾነ ነው የተናገሩት፡፡ ለሀገር እና ለሕዝብ ተቆርቁሮ ችግሮችን መፍታት ይገባልም ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎንደር ውኃ እንድታገኝ የሰጡትን መመሪያ በደስታ እንደተቀበሉት ነው የተናገሩት፡፡
ሌላኛው የጎንደር ከተማ ነዋሪ አቶ አዱኛ እሸቴ መገጭን አጠናቅቀን፣ የአንገረብን ግድብ ደለል አውጥተን፣ ጉድጓዱን ቆፍረን ውኃ እናቀርባለን ይባላል፤ ነገር ግን ሁሉም አልኾነም ይላሉ፡፡ በጎንደር ከተማ እጅግ አስከፊ ከሚባሉ ጉዳዮች አንዱ የውኃ ችግር ነው ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰሞኑ የሰጡት መመሪያ ጥሩ እንደኾነም አስረድተዋል፡፡
የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ (ዶ.ር) የጎንደር ከተማ የንጹሕ መጠጥ ውኃን በልዩ ሁኔታ ለማገዝ እየሠሩ መኾኑን አመላክተዋል፡፡ ቆመው የነበሩ የውኃ ጉድጓዶችን ችግር ለመፍታት በተደረገው ጥረት ከበፊቱ እንዲሻሻል ለማድረግ ተሞክሯል ነው ያሉት፡፡ በወር አንድ ጊዜ የነበረውን ውኃ ቢያንስ በሦስት ሳምንት እና በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ እንዲያገኙ መሻሻሎች ተደርገዋል ብለዋል፡፡
ተጨማሪ ጉድጓዶች መቆፈር በማስፈለጉ ሦስት ጉድጓዶችን ማስቆፈራቸውንም ገልጸዋል፡፡ ፓምፖችን የመግጠም ሥራ አለመሠራቱ ግን ክፍተት ነው ብለዋል፡፡ የተቆፈሩት ጉድጓዶች ወደ ሥራ ሲገቡ ተጨማሪ ኀይል እንደሚኾኑ ነው የተናገሩት፡፡ ተጨማሪ ሁለት ጎድጓዶች እንደሚቆፈሩም ገልጸዋል፡፡ ጎድጓዶቹ የመገጭ ግድብ እስኪጠናቀቅ እና የውኃ አቅርቦት እስኪቀርብ ድረስ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖራቸውም አብራርተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የመገጭ ውኃ ሲዘገይ የተጀመረው የጉድጓድ ቁፋሮ ያለበት ደረጃ ለሕዝቡ ግልጽ አለመኾኑንም አመላከተዋል፡፡ ሕዝቡ ከፍተኛ የውኃ ችግር እንዳለበበት ያነሳል ነው ያሉት፡፡ የውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ ጅማሮው ጥሩ ነው፤ ነገር ግን የጎንደር የውኃ እጥረት በተቆፈሩ ጉድጓዶች ሊሟላ አይችልም፣ ፍላጎቱ ከዚያ በላይ ነው ብለዋል፡፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ ከክልሉ መንግሥት ጋር በመተባበር የተቆፈሩ ጉድጓዶች ፓንፕ ተዘርግቶ ውኃ ለሕዝብ የሚደርስበትን መንገድ ፍጠሩ ብለዋቸዋል፡፡ የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ውኃ አድርሶ ሕዝብ ውኃ ይጠጣ ብለዋል፡፡
የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ደግሞ ውል ሰርዞ የመገጭ ግድብን ሥራውን ካስጀመረ በአንድ በኩል ውኃ እያጠጣን በሌላ በኩል ሥራ እየሠራ ነው ይህ ተስፋ ያጭራል ነው ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለቱም ሥራዎች ክትትል እንደሚያደርጉ ነው የተናገሩት፡፡ መልሰው ሲገመግሙ ቱቦ ተዘርግቶ ውኃ ለሕዝብ እየደረሰ ነው የሚል ሪፖርት እፈልጋለሁ ብለዋቸዋል፡፡ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ቃል ገብተውላቸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
