
ባሕር ዳር: ግንቦት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጎጃም ኮማንድፖስት በወቅታዊ የሰላም እና ፀጥታ እንዲሁም የልማት ሥራዎች ዙሪያ ባካሄደው መድረክ ላይ የቡሬ ከተማ ነዋሪዎች የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅ ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር በጋራ በመሰለፍ እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡
ነዋሪዎቹ ከዚህ በፊት ወቅታዊ ችግሮችን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው በዘረፋ ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላት ችግር ሲፈጥሩባቸው እንደነበር ጠቁመው ይህንን ችግር በማስወገድ ሰላምን ለማሥከበር ከጸጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሥራት ኀላፊነታቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።
ማንኛውም ጥያቄም ኾነ አለመግባባት በብረት ሳይኾን በውይይት ብቻ መፈታት አለበት ሲሉም ነዋሪዎች ገልጸዋል። የሕዝቡን ሰላም እና ደኅንነት ለመጠበቅ ቀን ከሌሊት እየሠራ ለሚገኘዎ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ታላቅ ክብር እና ምስጋና ይገባዋል ሲሉም አመስግነዋል።
የጎጃም ኮማንድፖስት ሰብሳቢ እና የምሥራቅ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጀነራል መሐመድ ተሰማ የተገኘው ሰላም በሠራዊቱ፣ በዞኑ መሥተዳድር እና አጋር የፀጥታ አካላት ጥምረት የመጣ ነው ብለዋል። ማኅበረሰቡ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር ዘላቂ ሰላም የማስፈን ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ የቡሬ አካባቢ ማኅበረሰብ ከጥምር የፀጥታ ኃይሉ እና ከመሥተዳድር አካላት ጋር ኾኖ በወሰዳቸው እርምጃዎች ወንጀለኞችን የመቆጣጠር ሥራው አመርቂ ውጤቶች ማስመዝገቡን ገልጸዋል። አሁን ላይ የቡሬ ከተማ እና አካባቢው በተሻለ የሰላም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በተደረጉ ስምሪቶች ጸረ-ሰላም ኃይሎችን በመደምሰስ ከፍተኛ ውድቀት ማድረስ ተችሏል፤ ይህ ውጤት የሠራዊቱን የማድረግ አቅም እና የሕዝቡን ትብብር ያመላከተ እና ትልቅ ድል የተመዘገበበት በመኾኑ ሕዝቡ የራሱን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ መሥራት እንደሚጠበቅበት መልእክት አስተላልፈዋል። ኮማንድፖስቱም የተጣለበትን ሕገ መንግስታዊ ተልዕኮ ለመወጣት በሚያደርገው ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ ሕዝቡ እንደ እስካሁኑ ሁሉ ወደፊትም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
