
ባሕር ዳር: ግንቦት 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል እንደገለጹት የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ሰፊ ሪፎርም እየተከናወነበት ነው። በሪፎርሙም መንግሥት በግልጽ ያስቀመጠው የዜጎች የክብር ጉዳይ መኾኑን አንስተዋል። በዚህም አንደኛው የዜጎችን እንግልት መቀነስ እና አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ መኾኑንን ገልጸዋል።
ሚኒስትሯ ባለፉት 10 ወራት 301 ሺህ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት እንዳደረጉ ገልጸዋል። የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ተጓዦች ወደማያውቁት ሀገር የሚሄዱ በመኾናቸው እንዲሰለጥኑ እና በቂ የሥነ-ልቦና ዝግጅት እንዲኖራቸው መደረጉን አመልክተዋል።
ይህ በጣም ትንሹ የሞራል ግዴታ መኾኑን ገልጸው፤ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት የማስጠበቅ መንግሥታዊ ግዴታውን እየተወጣ መኾኑን ሚኒስትሯ አንስተዋል።
ይሁን እንጂ ትክክለኛ ያልኾነ መረጃ ከመስጠት ጀምሮ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ የሚሳተፉ አካላት መኖራቸውን ተናግረዋል። ሂደቱ ሙሉ በሙሉ በአሠሪው መኾኑን እና ለክፍያ የሚጠየቁትም የፓስፖርት እና የጤና ምርመራ መኾኑን አንስተዋል። ከዚህ ውጪ ያሉ ክፍያዎች ሕገ-ወጥ መኾናቸውን እና በዚህ ድርጊት የሚሳተፉ አካላት በሰው ህይዎት መጫወት መኾኑን ተገንዝበው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
አሁን ላይ እየተተገበረ ያለው ቴክኖሎጂ የትኛውም በውጭ ሀገር ያለ ዜጋ የት እንዳለ ችግር ቢያጋጥማቸውም በአንድ ጥሪ ወደ ኤምባሲ መልዕክት የሚያስተላልፉበት መኾኑን ጠቁመዋል። ቴክኖሎጂው በሁሉም የውጭ የሥራ ስምሪት የሚያደርጉ ዜጎች ተደራሽ እንዲኾን ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር ስማርት ስልኮች የሚያገኙበት አሠራር እንዲኖር ውይይቶች እየተደረጉ መኾኑን ተናግረዋል።
ከቁጥሩ በላይም ትልቁ ነገር ክብራቸው እና ደኅንነታቸው በተጠበቀ መንገድ ጉዞ ማድረጋቸው መኾኑንም ሚኒስትሯ አመላክተዋል። በተቀባይ ሀገራትም ተቀባይ ኖሯቸው ያለምንም መጉላላት ወደ ሥራቸው የሚገቡበት አግባብ መፈጠሩን ገልጸዋል። ከተለያዩ ሀገራት ጋር አዳዲስ መዳረሻዎችን ለመክፈት እየተሠራ መኾኑን ገልጸው በተያዘው በጀት ዓመት ከሦስት ሀገራት ጋር ስምምነት ማድረግ የሚያስችሉ ውይይቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል። አሁንም የሚደረጉ ድርድሮች የዜጎችን መብት እና ጥቅም ያስጠበቁ መኾኑንም አመላክተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
