አካባቢን መጠበቅ እና መንከባከብ የተሻለ ማኅበረሰብን ለመፍጠር ያለው ሚና የጎላ መኾኑን የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ።

21

አዲስ አበባ: ግንቦት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም ከቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር የ2016 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እያካሄደ ነው። በዘጠኝ ወራት ሪፖርቱ ላይ እንደተገለጸው የሰው ልጅ በዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴው በተፈጥሮ ሃብት እንዲሁም በአካባቢ ላይ የሚያሳድራቸው አሉታዊ ተፅዕኖዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥተዋል፡፡

ይህንን ቁልፍ ችግር ለመቅረፍ ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት በርካታ ሥራዎች መሠራታቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል ። ባለፉት ዘጠኝ ወራት የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዜጎች ንፁህ እና የተመቸ የመኖሪያ አካባቢ እንዲኖራቸው ለማድረግ አካባቢን በመንከባከብ ተፈጥሯዊ ሚዛንን በመጠበቅ ችግኞችን በመትከል እና በመንከባከብ እንዲሁም ሌሎች ተዛማጅ ማኅበራዊ ጉዳዮችን በመፈፀም ረገድ የተሻለ ጥረት ማድረጉ በሪፖርቱ ተመላክቷል።

ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የአካባቢ ጥበቃ ቁጥጥር ሥርዓትን በማጠናከር በተለይ የፕላስቲክ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን በማዘመን ረገድ የተሠሩ ሥራዎች የተሻለ አፈፃፀም የታየባቸው መኾኑ ተገልጿል። በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጣውን ችግር ለመግታት የአካባቢ ብክለትን በሁሉም ዘርፍ በመከላከል ለዜጎች ምቹ አካባቢን ለመፍጠር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን በትኩረት በመሥራት የተሻለ እና ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉም ተመላክቷል።

የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ የፕላስቲክ፣ የአየር፣ የውኃ፣ የአፈር እና የድምጽ ብክለትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎች በተሻለ ደረጃ መሠራታቸው ተነስቷል። በአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተሠሩ ሥራዎች አበረታች ሲኾኑ በተወያዮች በሥራ ላይ ያጋጠሙ ችግሮች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በውይይቱም የመፍትሄ ሃሳቦች ቀርበው በቀሪ ጊዜያት ችግሮችን በመቅረፍ የተሻለ ሥራ ለመሥራት መግባባት ላይ ተደርሷል።

ዘጋቢ:- ሰለሞን አሰፌ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሕዝብ መገናኛ ብዙኀን የኅብረተሰቡን ባሕል እና እሴት በማይቃረን መልኩ እንዲሠሩ በቴክኖሎጂ የታገዘ የክትትል ሥራ እየተሠራ ነው” የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን
Next articleበውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ሪፎርም ውስጥ የዜጎች የክብር ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል።