“የዓለም የፋይናንስ ሥርዓተ በተረጋጋ ሁኔታ እንዳይቀጥል የሳይበር ጥቃት ችግር ደቅኖበታል” የዓለም የገንዘብ ተቋም

23

ባሕር ዳር: ግንቦት 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የዓለም የገንዘብ ተቋም ሪፖርት እንደሚያመለክተው የሳይበር ጥቃት ድግግሞሹ እና ውስብስብነቱ እያደገ መምጣቱ ስጋቱን አደገኛ አድርጎታል ብሏል። በዓለም የምጣኔ ሃብት ፎረም ማዕከል የኢንዱስትሪ እና አጋርነት ኀላፊ የኾኑት አክሻይ ጆሺ የሳይበር ጥቃት እያደገ የመጣ ሲኾን በፋይናንስ ዘርፍ ላይ የሚፈፀመው የጥቃት ሙከራ ድግግሞሽ እና ውስብስብነቱ ከፍ ያለ ነው ብለዋል።

የፋይናንስ ዘርፉ በጣም ሰፊ የኾነ ሚስጥራዊ መረጃ እና ልውውጥ የሚደረግበት በመኾኑ በልዩ ሁኔታ ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ እንደሚያደርገው ሪፖርቱ ያብራራል። ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ከተፈፀሙት የሳይበር ጥቃቶች ውስጥ አንድ አምስተኛ የሚኾኑት በዓለም የፋይናንስ ዘርፍ ላይ የተፈጸሙ ናቸው ተብሏል። 12 ቢሊዮን ዶላር ቀጥተኛ ኪሳራ እንዳደረሱም ተነግሯል። እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2020 ወዲህ ደግሞ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ቀጥተኛ ኪሳራ ማድረሱን የዓለም የገንዘብ ተቋም ሪፖርት ያሳያል።

የገንዘብ ተቋሙ የፋይናንስ ዘርፉ የሳይበር ደኅንነት አቅሙን ማሳደግ እንዳለበት እና ሀገራት ደግሞ በቂ የኾነ የሳይበር ደኅንነት ስትራቴጂ መቅረጽ እንደሚኖርባቸው አሳስቧል። ችግሩን ለመከላከል የፖሊሲ እና አስተዳደር ማዕቀፍ ማዘጋጃት ወሳኝ መኾኑም በሪፖርቱ ተመላክቷል። በአብዛኛው ጥቃቶች የሚፈጸሙት የገንዘብ ተቋማት ከሚገኙበት ሀገር ውጭ በመኾኑ የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል ዓለም አቀፍ ትብብር እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየስኳር በሽታ!
Next articleየሕዝብ መገናኛ ብዙኀን የኅብረተሰቡን ባሕል እና እሴት በማይቃረን መልኩ እንዲሠሩ በቴክኖሎጂ የታገዘ የክትትል ሥራ እየተሠራ ነው” የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን