የስኳር በሽታ!

63

ባሕር ዳር: ግንቦት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የስኳር በሽታ ተላላፊ ካልኾኑ በሽታዎች ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፉ ከሚገኙ በሽታዎች ውስጥ አንዱ ነው። በሽታው በደም ውስጥ ከመጠን ያለፈ ስኳር ሲፈጠር የሚከሰት ነው። መንስኤው በግልጽ ባይታወቅም በተፈጥሮ ቆሽት (ፓንክሪያስ) እየተባለ በሚጠራው የሰውነት ክፍል ውስጥ የሚመነጨው ኢንሱሊን በበቂ ሁኔታ አለመመንጨት፣ ኢንሱሊኑ በተለያየ ምክንያት ሲጎዳ ማመንጨት ሲያቆም እና በቂ ኢንሱሊን መንጭቶ በአግባቡ ባለመሥራቱ ምክንያት ሊከሰት እንደሚችል በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቤተሰብ ሕክምና ስፔሻሊስት ሀኪም ሰፊ ድልነሳ (ዶ.ር) ገልጸዋል። ኢንሱሊን ሥራ ከምግብ የሚገኘውን ግሉኮዝ ወይንም ስኳር ወደ ተለያዩ ሰውነት ክፍሎች ተሰራጭቶ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ነው፡፡

ታዲያ ሰውነት በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን መቆጣጠር ሲሳነው ቋሚ የኾነ የስኳር መጨመር ይከሰታል። ይህም የስኳር ሕመምን ያስከትላል። የስኳር በሽታ አራት አይነት ሲኾን ከእነዚህ ውስጥ ዓይነት አንድ አንዱ ነው። ብዙን ጊዜ በወጣትነት በተለይም ደግሞ ከ30 ዓመት በታች ሊከሰት የሚችል በሽታ ነው። መንስኤው በውል ባይታወቅም የኢንሱሊን አለመመረት ወይንም እጥረት ምክንያት የሚከሰት በሽታ ነው።

ሰውነት ማምረት ያቆመውን ኢንሱሊን ለመተካት የአካል ብቃት እና አመጋገብን ባመጣጠነ መንገድ በቋሚነት በመርፌ መስጠት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል። ሁለተኛው የስኳር በሽታ ዓይነት ሁለት እየተባለ ይጠራል። በሽታው በጎልማሶች እና በአዛውንቶች ላይ የሚከሰት የበሽታ ዓይነት ነው። በብዛት ጤናማ ባልኾነ አመጋገብ፣ ብዙ ጊዜ በመቀመጥ፣ በማጨስ፣ አልኮል በመጠጣት በመሳሰሉ ምክንያቶች ይከሰታል። የቅርብ ቤተሰብ የስኳር በሽታ ካለባቸው በበሽታው የመጋለጥ እድሉ ከፍተኛ ነው።

ሦስተኛው በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር በሽታ ነው። ይህ በእርግዝና ጊዜ በደም ውስጥ ስኳር በሚጨምርበት ጊዜ የሚከሰት በሽታ ነው። በወቅቱ ሕክምና ካልተደረገ በእናት እና በጽንሱ ጤንነት ላይ አደጋ ያስከትላል። አራተኛው ደግሞ በተለያዩ መድኃኒቶች ምክንያት የሚከሰት በሽታ ሲኾን ጊዜያዊ ሊኾን ይችላል። መድኃኒቱ በሚቆምበት ወቅት በሽታውም አብሮ ሊጠፋ ወይንም ቀጣይነት ሊኖረው ስለሚችል ክትትል ማድረግ ይገባል። በተለያዩ በሽታዎች ምክንያት ከተከሰተም በሽታው ሲድን አብሮ ሊጠፋ ይችላል።

የስኳር በሽታ ዋና ምልክቶች፦
👉 ከሌላ ጊዜ የበለጠ በብዛት እና ቶሎ ቶሎ መራብ
👉 የማያቋርጥ የውኃ ጥም ወይንም ቶሎ ቶሎ የሚከሰት የውኃ ጥም እና በብዛት መጠጣት
👉 ብዙ ጊዜ መሽናት ወይንም በቀን እና በሌሊት ቶሎ ቶሎ የሚመጣ ሽንት ዋና ዋናዎቹ ምልክቶች ናቸው። በተጨማሪም ምክንያቱ ያልታወቅ ድካም፣ ሰውነት ላይ በቀላሉ የማይድን ቁስለት፣ የዓይን ችግር፣ የቆዳ መድረቅ፣ ድንገተኛ የክብደት መቀነስ የመሳሰሉ ምልክቶች ሊከሰቱ ይችላሉ።

በሽታውን ከምግብ በፊት እና ከምግብ በኋላ ከጣት ላይ ደም በመውሰድ ምርመራ በማድረግ መለየት ይቻላል። ከምግብ በፊት ጤናማ የኾነ ሰው የደም ስኳር ሲለካ ከ110 በታች ሊኾን ይገባል። ከ 110 እስከ 126 ከኾነ ወደፊት ለስኳር በሽታ የመጋለጥ እድሉ ከፍተኛ በመኾኑ ቅድመ ስኳር በሽታ ክትትል እንዲያደርግ ይመከራል። ከምግብ በኋላ ሲለካ ደግሞ ከ180 በታች እንዲኾን ይመከራል። ሁለተኛው ምርመራ “ኤ ዋን ሲ” እየተባለ የሚጠራው ሲኾን ደም በመውሰድ የሚደረግ ምርመራ ነው። ከ6 ነጥብ 5 በመቶ በታች ከኾነ ጤናማ ተደርጎ ይወሰዳል።
የስኳር በሽታ ሕክምና

የስኳር በሽታን ፈጽሞ ማዳን ወይንም እንዳይከሰት ማድረግ ባይቻልም አጋላጭ ምክንያቶችን መቀነስ እንደሚቻል ዶክተር ሰፊ ገልጸዋል።
👉 የስኳር ታማሚ በሐኪም የታዘዘለትን መድኃኒት (በተለይ ኢንሱሊን) በየጊዜው ተከታትሎ መውሰድ ይጠበቅበታል።
👉 በፋብሪካ ታሽገው የሚመጡ እንደ ፓስታ፣ ማኮሮኒ የመሳሰሉ ምግቦች አለማዘውተር
👉 ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል።

አመጋገብ ምን መምሰል አለበት?

አንድ የስኳር ታማሚ የተመጣጠነ ምግብ እንዲመገብ ይመከራል። የስኳር ታካሚው ማዕድ በሚቀርብበት ጊዜ የሳህኑ ግማሽ ስታርች የሌላቸው እንደ አረንጓዴ አትክልት እና በመጠኑ ፍራፍሬ፣ የሳህኑ ሩብ ካርቦ ሃይድሬት (ስታርች) ያላቸው፣ ሩቡ ደግሞ ፕሮቲን ያላቸውን ምግቦችን እንዲመገብ ይመከራል።
ከዚህም ባለፈ ቅቤ፣ ቅባትነት እና ጣፋጭነት ያላቸው ነገሮችን መቀነስ ይገባል። ሲጋራ ከማጨስ እና አልኮል ከመውሰድ መታቀብ፣ መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ክብደት መቀነስ፣ የስኳር በሽታ መድኃኒቶችን በአግባቡ ሳያቋርጡ መውሰድ ይገባል።

አንድ የስኳር በሽተኛ የማዞር፣ ማቅለሽለሽ፣ ላብላብ ማለት ምልክቶች እንደተከሰቱ ጤና ተቋም እስኪደርስ እንደ ከረሚላ፣ ስኳር፣ ሚሪንዳ የመሳሰሉ ጣፋጭ ነገሮችን እንዲወስዱ ይመከራል። ከዚህ ባለፈ በየቀጠሮው ጤንነቱን መታየት፣ በሰውነት ውስጥ ያለን የኮሊስትሮል መጠን ክትትል ማድረግ ወይንም መለካት፣ ዓይን፣ እግርን፣ ኩላሊትን፣ ግፊትን በጤና ባለሙያ በየጊዜው ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል።

ከመጠን ያለፈ ውፍረት እና በተለያዩ ምክንያቶች አካላዊ እንቅስቃሴያቸው የተገደቡ ሰዎች፣ የስኳር ሕመም የቅርብ ቤተሰብ ያላቸው ሰዎች፣ በእርግዝና ጊዜ ስኳር መጨመር የታየባቸው እናቶች እና ክብደታቸው ከ4 ኪሎ ግራም በላይ የወለዱ እናቶች ከኾኑ የቅድመ ስኳር ሕመም ምርመራ ማድረግ አለባቸው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሕዝቡ አንድነቱን እና ሰላሙን በመጠበቅ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ውጤታማ እንዲኾኑ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ
Next article“የዓለም የፋይናንስ ሥርዓተ በተረጋጋ ሁኔታ እንዳይቀጥል የሳይበር ጥቃት ችግር ደቅኖበታል” የዓለም የገንዘብ ተቋም