ፅዱ፣ ውብ እና ለነዋሪዎች ተስማሚ ከተሞችን ለመፍጠር ኅብረተሰቡ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ ሥርዓትን ማዘመን እንደሚገባው ተገለጸ።

21

እንጅባራ: ግንቦት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አካባቢ እና ደን ጥበቃ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የእንጅባራ ከተማን ጽዱ ለማድረግ በቀጣይ ስድስት ወራት በሚተገበሩ ሥራዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርጓል። በምክክር መድረኩ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪና የከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ አይተነው ታዴ ከተማን በፕላን ለመምራት፣ መሬትን በአግባቡ ለማሥተዳደር፣ ተወዳዳሪ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለመገንባት ፅዳት እና ውበትን መጠበቅ አስፈላጊ መኾኑን ገልጸዋል።

በእንጅባራ ከተማ ወጣቶችን በማደራጀት ደረቅ ቆሻሻን የማሰወገድ መልካም ጅምሮች ቢኖሩም የቆሻሻ ማስወገጃ ስፍራዎቹ ደኅንነታቸው አለመጠበቅ ለአካባቢ ብክለት ምክንያት መኾኑንም ገልጸዋል። ፅዱ፣ ውብ እና ለነዋሪዎች ተስማሚ ከተሞችን ለመፍጠር ኅብረተሰቡ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ ሥርዓትን ማዘመን እንደሚገባውም አቶ አይተነው አስገንዝበዋል።

የብሔረሰብ አሥተዳደር አካባቢና ደን ጥበቃ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቤዛዊት ጌታሁን በዘፈቀደ የሚወገደው ደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻ የከተሞችን እድገት እየገታ፣ በተወዳዳሪነታቸው ላይም ተፅዕኖ እያሳደረ መኾኑን ነው ያነሱት። እንጅባራ ከተማን ፅዱ እና ለነዋሪዎቿ ተስማሚ ለማድረግ የቀጣይ ስድስት ወራት የድርጊት መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱንም ገልጸዋል።

የእንጅባራ ከተማ ነዋሪዎችም በከተማዋ የሚፈስሱ ወንዞች ለከተማዋ ተጨማሪ የውበት ምንጭ መኾን ሲገባቸው የቆሻሻ ማስወገጃ እየኾኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል። የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ የኔዓለም ዋሴ በከተማዋ የሚስተዋለውን የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ደረቅ ቆሻሻን ወደ ገቢ ለመቀየር የቀረቡ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

ከተማ አሥተዳደሩ በደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ ላይ በነዋሪው ዘንድ የሚስተዋሉ የተዛነፉ አመለካከቶችን ለማስተካከል በተዋረድ ባሉ ምክር ቤቶች አስገዳጅ ደንቦችን በማውጣት ሥርዓት ለማስያዝ ዝግጅት እየተደረገ እንደኾነም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል።

ዘጋቢ:–ሳሙኤል አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የጎንደር ሕዝብ መንገዱ ይጠናቃቃል በሚል ተስፋ ለዓመታት በትዕግሥት ጠብቋል” የጎንደር ከተማ ነዋሪ
Next article“ሕዝቡ አንድነቱን እና ሰላሙን በመጠበቅ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ውጤታማ እንዲኾኑ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ