“የጎንደር ሕዝብ መንገዱ ይጠናቃቃል በሚል ተስፋ ለዓመታት በትዕግሥት ጠብቋል” የጎንደር ከተማ ነዋሪ

55

ባሕር ዳር: ግንቦት 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የውስጥ ለውስጥ መንገድ ይሠራልን ጥያቄ ለዓመታት የዘለቀ ነው፡፡ በከተማዋ የሚነሳውን የመንግድ ይሠራልን ጥያቄ ይመልሳል የተባለለት የአዘዞ ብልኮ (አርበኞች አደባባይ) የመንገድ ሥራ ከተጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ነገር ግን መንገዱ በሚፈለገው ፍጥነት ባለመሠራቱ የከተማዋን ነዋሪዎች ለምሬት ዳርጓል፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች መንገዱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ እና ለአገልገሎት ክፍት እንዲኾን በተዳጋጋሚ የሚመለከታቸውን ሁሉ ጠይቀዋል፤ ምንም እንኳን ጥያቄያቸው በቂ ምላሽ ሳይሰጠው ዓመታት ቢቆጠሩም፡፡ ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በጎንደር ከተማ የሚገኙ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ የሥራ መመሪያ መስጠታቸውን ተከትሎ የመንገዱ ጉዳይ እልባት ሊያገኝ ይችላል የሚል አዲስ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

የአዘዞ ብልኮ መንግድ ሥራ ፕሮጀክት አስተባባሪ እና የሕዝብ ተወካይ ዳንኤል ከበደ የመንገድ ሥራው እንቅስቃሴ የተጀመረው በ2009 ዓ.ም እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ነገር ግን የሦስተኛ ወገን ችግር ስለነበረበት እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ ያለ ምንም ሥራ ባለበት መቆየቱን ነው የገለጹት፡፡ ኅዳር 2011 ዓ.ም ግን ሥራው መጀመሩን አንስተዋል፡፡ የመንገድ ሥራ ጥራት ችግር የለበትም የሚሉት ተወካዩ መዘግየቱ ግን የሕዝብ ጥያቄ ኾኖ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰሞኑ የሰጡት የሥራ መመሪያ መንገዱ እንዲጠናቀቅ የሚያስችል መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የጎንደር ሕዝብ መንገዱ ይጠናቃቃል በሚል ተስፋ ለዓመታት በትዕግሥት ጠብቋል ነው ያሉት፡፡ መንገዱ ተጀምሮ ለዓመታት በመቆየቱ ነዋሪዎች እንደአሻቸው እንዳይንቀሳቀሱ አድርጓል፡፡ ወላዶች ወደ ሕክምና፣ ተማሪዎችም ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ እንደሚቸገሩ ነው የገለጹት፡፡ የተቆፈረው መንገድ ገደል በመኾኑ አቅመ ደካሞች ከቤታቸው እንዳይወጡም አድርጓል፤ ይህ ሁሉ ማኅበራዊ ችግር ባለበት፣ ጥንታዊ እና ታሪካዊ በኾነች ከተማ ውስጥ መንገዱን ለመጨረስ ረጅም ዓመታትን መውሰድ እንዳልነበረበትም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የነበረውን በማሻሻል ቋጭቶ መንገዱን ለጎንደር ሕዝብ ክፍት ማድረግ ይገባልም ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወሰኑት ውሳኔ አስደስቶናል፤ ፕሮጀክቱን ከሚሠሩት ተቋራጮች ጋር በጋራ ኾነን ማገዝ አለብን ነው ያሉት፡፡ የከተማ አስተዳደሩ መሪዎችም በቁርጠኝነት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በጎንደር ከተማ የሚፈጸሙ ፕሮጀክቶችን በገመገሙበት ወቅት የሰጡትን የሥራ መመሪያ አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሐመድ አብዱራህማን የአዘዞ ብልኮ የአስፓልት መንገድ መጓተት እንደገጠመው ገልጸዋል፡፡ በ2016 ዓ.ም 4 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመሥራት አቅደው የተሠራው ሥራ 0 ነጥብ 1 በመቶ የማይሞላ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡

የሥራ ተቋራጩ የአቅም ማነስ፣ የገንዘብ ችግር እና ሌሎች ችግሮች ለአፈጻጸሙ ማነስ እንደምክንያት ተቀምጠዋል፡፡ በቀጣይ ወራት 9 ነጥብ 8 በመቶ የውኃ ማፋሰሻ ቦዮችን እና በቀሩት ሁለት ኪሎ ሜትሮች ላይ የአፈር ቆረጣና ሙሌት ለመሥራት ማቀዳቸውንም ገልጸዋል፡፡ 4 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የአስፓልት ንጣፍ ለመጨረስም ማቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡ በቀሪ ወራት የመንገዱን ቀሪ ሥራዎች ለማጠናቀቅ እየሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በጎርጎራ እና በባሕር ዳር በነበራቸው ቆይታ በአንዳንድ ሥራዎች ፈጣን እና ውጤታማ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል፡፡ ጎንደር ላይ የተጓተቱ እና ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ ሦስት ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ በሕዝብ ዘንድ ምሬት ከፈጠሩ ፕሮጀክቶች መካከል ከአዘዞ ብልኮ እየተሠራ ያለው የመንገድ ፕሮጀክት አንዱ መኾኑን አንስተዋል፡፡ ለሕዝብ የሚገቡ ቃሎችን በትጋት ሠርቶ መጨረስ መለያችን ስለኾነ ምላሽ መስጠት አለብን ብለዋል፡፡

የሀገር እድገት እና የሚታሰበው ለውጥ የሚመጣው በፕሮጀክቶች ስኬት መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የፕሮጀክቶች ድምር ፕሮግራም ያሳካል፤ የፕሮግራም ድምር ደግሞ ሕልማችንን ያሳካል፤ በፕሮጀክት ደረጃ የሚሰጠው አመራር የፕሮግራም ስኬትን እና ሀገራዊ ስኬትን ይወስናል ነው ያሉት፡፡ ፕሮጀክት በባሕሪው በቂ ጥናት እና እውቀት እንደሚፈልግም አስገንዝበዋል፡፡ አደጋዎችን የመለየት እና ለማስቀረት የሚያስችሉ አማራጮችን መያዝ እንደሚፈልግም አመላክተዋል፡፡

ፕሮጀክትን ለመፈጸም የሚያስችል ሃብት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል፡፡ አመራር፣ የክትትል ሥራ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንቅፋቶችን እየፈቱ፣ ድጋፍ እያደረጉ መሄድ ካልተቻለ በጀት ስለተያዘ እና ውል ስለተፈረመ ብቻ ከግብ ሊደርስ አይችልም ብለዋል፡፡ ተጀምሮ ከሚቀር ፕሮጀክት ያልተጀመረ ፕሮጀክት ይሻላል ነው ያሉት፡፡ አንድ ፕሮጀክት ጀምሮ በጊዜው አለማጠናቀቅ እንደ ሀገር ከፍተኛ እዳ ኾኖብናልም ብለዋል፡፡

ችግሮችን በመገንዘብ ወጣ ያለ የአመራር ብቃት፣ አቅም፣ ከትትል ካላሳየን በስተቀር እያንዳንዱ ሥራ ተጨማሪ ችግር እና እዳ እንደሚያመጣ መኾኑን መገንዘብ ይቻላል ነው ያሉት፡፡ የአዘዞ ብልኮን መንገድ በተመለከተ ሲያብራሩ 27 ሺህ እና 28 ሺህ ኬሎ ሜትር መንገድ በሚሠራ ሀገር 10 ኪሎ ሜትር መንገድ መሥራት የሚያስቸግር አለመኾኑን ገልጸዋል፡፡ የመንገዱን ሥራ ያወሳሰበው ከተማ ውስጥ መኾኑ፣ መልከዓ ምድሩ እና የተቋራጩ አቅም ሊኾን ይችላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቋራጮች ከአቅማቸው በላይ ሥራ ወስደው፣ እነርሱም ሳይጠቀሙ፣ ሥራውንም ሳይጨርሱ ሕዝቡም ተማርሮ ከሁሉ ያጣ እየኾን ነው ብለዋል፡፡ በሰጡት መመሪያም በአንድ ሳምንት ውስጥ ውሉ እንዲቋረጥ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የቀረውን ሥራ በጥቂት ወራት ውስጥ በከፍተኛ ርብርብ እንዲያጠናቅቅ አሳስበዋል፡፡ ተጨማሪ ሃብት እና አመራር እንደሚፈልግም ገልጸዋል፡፡

ለጊዜ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ ያሳሱበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስድስት ወር መጠናቀቅ የሚገባውን መንገድ ወደ ዘጠኝ ወር ቢራዘም ለሦስት ወር ችግር እና ምሬት ተራዝሟል ማለት ነው፤ ባጠረ ጊዜ መጠናቀቅ አለበት፣ ጊዜው ስላጠረ ደግሞ ጥራቱ መዘንጋት የለበትም፣ ይህ እንዲኾን ክትትል ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴርም ድጋፍ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትም ክትትል እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

ሕዝቡ ብዙ ነገር ይጠብቃል፤ በሌሎች አካባቢዎች ያመጣናቸው ውጤቶች በዚያ አልታዩም፣ በእነዚህ ሥራዎች ሕዝቡን መካስ፣ ምሬቱን መቀነስ፣ ልንሠራለት እንደምንችልን፣ ፍላጎት እንዳለን ማሳየት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ሥራው ሲሠራ የሕዝብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ሕዝቡ ሰላሙን በመጠበቅ የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም እንዲደግፍ አሳስበዋል፡፡ በሥራው ላይ የሚሳተፉ ሠራተኞችም ለሕዝባቸው ውኃ እና መንገድ እያቀረቡ መኾናቸውን አስበው ተጨማሪ አቅም መጠቀም ያስፈልጋቸዋል፤ በስምንት ሰዓት ሥራ ማሳካት አይቻልም፤ በሁለት በሦስት ፈረቃ ቀንም ማታም ሰርተን ነው የምናሳከው ብለዋል፡፡ የክልሉ መሪዎች ድጋፍ እና ክትትል እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ ተባብረን የተለመደውን በውጤት ሕዝብን የማርካት ተግባር እንድንፈጽም አደራ እላለሁም ነው ያሉት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በቤት ልማት ዙሪያ በጋራ ለመሥራት ተስማሙ።
Next articleፅዱ፣ ውብ እና ለነዋሪዎች ተስማሚ ከተሞችን ለመፍጠር ኅብረተሰቡ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ ሥርዓትን ማዘመን እንደሚገባው ተገለጸ።