የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በቤት ልማት ዙሪያ በጋራ ለመሥራት ተስማሙ።

36

ባሕር ዳር: ግንቦት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በቤት ልማት ዙሪያ በጋራ ለመሥራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ተስማሙ። በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የተመራው እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ረሻድ ከማልን ያካተተው የፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የልዑካን ቡድን በቤት ልማት ዙሪያ ባካሄደው ምክክር የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በጋራ ለመሥራት በአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ ስምምነት ላይ ደርሰዋል ፡፡

የልዑካን ቡድኑ አባል የኾኑት የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ረሻድ ከማል አቻ ከሆነው ተቋም ከአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ሰፊ ምክክርና ውይይት አድርገዋል፡፡ የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ በመንግሥት መነሻ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ ድጋፍ ተደርጎለት የሚገነባቸውን ቤቶች ከ30 በመቶ እስከ 40 በመቶ ከገበያው የዋጋ ቅናሽ ያላቸውን ቤቶች በሽያጭ እያቀረበ ገበያ የማረጋጋት ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ተጠቅሷል፡፡

የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ ከመንግሥት የሚያገኘውን መነሻ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ገበያ ለመረጋጋት ለሚገነባቸው ቤቶች ግንባታ የሚያውል ሲኾን ያገኘውን የበጀት ድጋፍ ለመንግሥት የመመለስ ግዴታ የሌለበት ተቋም እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከቅረብ ጊዜ ወዲህ የሪል ስቴት ገበያውን ለማረጋጋት እያደረገ ላለው ጥረት የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ ያለውን ሰፊ ልምድ ለፌዴራል ቤቶች የሚጋራ ይኾናል፡፡ የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲን ልምድና ተሞክሮ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሠራም ታውቋል፡፡

የቀድሞው ኪራይ ቤቶች የአሁኑ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጠንካራ መንግሥታዊ የሪል ስቴት ካምፓኒ ለመሆን በሚያስችለው አግባብ እየደረጀ ሲኾን የሪል ስቴት ገበያው እንዲረጋጋ የራሱን ሚና እየተጫወተ ስለመኾኑ ከኮርፖሬሽኑ የተገኘ መረጃ አመላክቷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጦርነት መፍትሔ አይደለም፤ ሰላም እንፈልጋለን” የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት
Next article“የጎንደር ሕዝብ መንገዱ ይጠናቃቃል በሚል ተስፋ ለዓመታት በትዕግሥት ጠብቋል” የጎንደር ከተማ ነዋሪ