በከተሞች የሚለጠፉ ማስታወቂያዎች የከተማ ገጽታ እያበላሹ እንደኾነ ተገለጸ፡፡

28

ደብረ ብርሃን: ግንቦት 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በከተሞች የሚለጠፉ ማስታወቂያዎች ገጽታ እንዳያበላሹ እየተሠራ መኾኑን የደሴ እና ደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች ተናግረዋል፡፡ በኢፌዴሪ የማስታወቂያ አዋጅ ቁጥር 759/2012 መሠረት ማስታወቂያ ሲሠራ ክልከላዎችን በማይተላለፍ መልኩ መኾን እንዳለበት ያስቀምጣል።

በተለይ ማንኛውም የውጭ ማስታወቂያ ከመንገድ አቅጣጫ ጠቋሚ ምልክት ጋር በሚመሳሰል፣ እይታን በሚጋርድ፣ የትራፊክ እንቅስቃሴን በሚገታ ወይም የአካባቢን ገጽታ እና ውበት በሚያበላሽ መልኩ መቀመጥ እንደሌለበት አዋጁ ያስቀምጣል፡፡ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ወርቃለማሁ ኮስትሬ እንደሚሉት የውጪ ማስታወቂያዎች የከተማውን ገጽታ የሚያበላሹ ናቸው፡፡

ለእይታ የሚጎረብጡ፣ የቀለም እና ቋንቋ አጠቃቀማቸው ያልተስተካከለ፣ የሕዝቡን ማኅበራዊ እንቅስቃሴ የሚጎዱ መኾናቸውንም ነግረውናል፡፡ ይኽም ከግንዛቤ እጥረት የተፈጠረ ስለመኾኑ ጠቁመዋል፡፡ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር በተለይም በኮሪደር ልማት የከተማዋን ውበት ለማሳመር እየሠራ ሲኾን ሥራው ውጤታማ እንዲኾን የከተሞችን ልምድ እንደወሰዱ ተናግረዋል፡፡

የማስታወቂያ ሥራ በሥርዓት ካልተመራ በስተቀር የማኅበረሰቡን መብት እና ጥቅም እንዲሁም ከባቢያዊ ገጽታ ሊጎዳ የሚችል በመኾኑ መብትን በአግባቡ መጠቀም እና ግዴታን መወጣት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የደሴ ከተማ አሥተዳደር በማስታወቂያ አለጣጠፍ ላይ ተሞክሮ የሚኾን ሥራ እንዳለው የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ከአማራ ኤፍ ኤም ደብረ ብርሃን 91 ነጥብ 4 የራዲዮ ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ መሠረተ ልማት ከማሟላት ባሻገር የከተማዋን ውበት ማስጠበቅ ትኩረት ተሰጥቶታል ነው ያሉት፡፡ አሁን ላይ አግባብ ባልኾነ መንገድ የተደረቱ ማስታወቂያዎችን ከማጽዳት ጀምሮ ሕንጻዎች ማራኪ እይታ እንዲኖራቸው ቀለም የመቀባት ሥራ ተጀምሯል ብለዋል፡፡

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው እንዳሉት ይኽ ተግባር አሁን ላይ በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ እየተተገበረ ነው፡፡ ከተማ አሥተዳደሩ ደግሞ በቀጣይ ምዕራፍ የሚከናወኑ ተግባራት ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሠራ ነው፡፡ በተለይ የስማርት ሲቲ ጽንሰ ሀሳብን ለመተግበር የመልሶ ልማት ትግበራን የተመለከቱ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡ በግንቦት ወር መጨረሻ ቀናትም ጽዱ ደሴን የመሥራት ተግባሩ ይጠናቀቃል ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡-ደጀኔ በቀለ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ የኀብረት ሥራ ማኀበራትን ውጤታማ ለማድረግ አቅማቸውን ማጎልበት እንደሚገባ ተገለጸ።
Next article“ጦርነት መፍትሔ አይደለም፤ ሰላም እንፈልጋለን” የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት