
ባሕር ዳር: ግንቦት 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የውጭ ሀገር ዜጎች የሥራ ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያ 29/2012 ትግበራ ዙሪያ ውይይት አካሂዷል። የኮንስትራክሽን ዘርፉ ያሉትን አማራጮች እና አሁናዊ ቅርጽ ላይ በመመካከር ጠቃሚ ሃሳቦችን ማመንጨት በማስፈለጉ ውይይቱ አስፈላጊ አንደኾነ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒሰቴር ዴኤታ ኢንጅነር ወንደሙ ሴታ ተናግረዋል።
ዘርፉ ትብብር እና መረዳዳት ያስፈልጉታል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው መመሪያው ተጠያቂነትን እና አሳታፊነትን እንዴት ማምጣት ይቻላል የሚለውን ይዳስሳል ብለዋል። በጋራ ኾነን ለሀገራችን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የተሻለ ልዩነት መፍጠር እንችላለን ነው ያሉት።
የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት ኢንጂነር ጠንክር መኩሪያ በአራት ምክንያቶች መመሪያ ማውጣት እንዳስፈለገ አስረድተዋል።
የመመሪያውን ማውጣት ምክንያቶች ሲያብራሩ፦
✍️ ከብዙ ዘርፎች ጋር በጋራ የሚሠራ በመኾኑ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የሥራ እና የሙያ ግንኙነቶችን ለመወሰን በማስፈለጉ
✍️ ዘርፉ በብዙ ችግሮች የተያዘ በመኾኑ አማራጭ ለማየት እና የዕውቀት ሽግግር መኖሩን ለማረጋገጥ
✍️ የውጭ ሀገር ሠራተኞችን እና ተቋማትን የሥራ ፍቃድ ለመስጠት በማሰብ እና ስምሪቱም በሀገር ውስጥ በሙያተኞች የማይሸፈኑ መኾናቸውን አረጋግጦ መስጠት በማስፈለጉ
✍️ እንዲሁም የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ እና እሱም በአግባቡ እና በአጭር ጊዜ እንዲከናወን ለማድረግ መመሪያው አስፈልጓል ብለዋል።
ይህ መመሪያ የወጣው በ2012 ዓ.ም ቢኾንም ወደ ትግበራ ሳይገባ በመቆየቱ ለመተግበር አንቅስቃሴ ላይ የተገባ ሲኾን ከሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር ልዩ ትብብር እየተደረገ ነው ተብሏል።
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
