
ባሕር ዳር: ግንቦት 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ለባለሃብቶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር፣ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት፣ በዘርፉ እያጋጠሙ ባሉ ማነቆዎች እና በመፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ውይይት ተደርጎ አቅጣጫ ተቀምጧል። ባለድርሻ አካላትም መሠረተ ልማት በማሟላት፣ ሥልጠና በመስጠት እና የገንዘብ አቅርቦትን በማሳለጥ ኢንቨስትመንቱን እንደሚያግዙ ሃሳብ ሰጥተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ለተነሱ አስተያየቶች፣ ጥያቄዎች እና ችግሮች ከተማ አሥተዳደሩ ለመፍትሄ እንደሚሠራ ተናግረዋል። ያደሩ ችግሮችን ለመፍታት ለሚቀርቡ የልማት ፕሮጀክቶች ፈጣን ምላሽ እንደሚሰጥም ገልጸዋል። መንገድ እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ነው ከንቲባው ያመላከቱት።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ባለሃብቶች የወሰዱትን መሬት በአግባቡ እንዲያለሙ እና የማኅበራዊ ልማት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል። የውይይቱ የክብር እንግዳ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ የክልሉን ኢንቨስትመንት ለማነቃቃት ሰፊ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በ11 ዞኖች፣ በ48 ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ከባለሃብቶች ጋር ውይይት መደረጉንም ጠቅሰዋል።
በክልሉ ያለውን የኢንቨስትመንት አቅም ለመጠቀም ፍኖተ ካርታ እና አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚስተናገዱበትን የተለየ አሠራር መዘጋጀቱን ገልጸዋል። በደላላ እና ጉዳይ አስፈጻሚ ላይ ያለውን አመለካከት በመስበር ፈጣን እና ሕጋዊ አገልግሎት ለመሥጠት በመንግሥት በኩል ዝግጁነት መኖሩን አብራርተዋል።
ለባሕር ዳር ከተማ ብቻ ለመሠረተ ልማት ግንባታ ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን የጠቀሱት ቢሮ ኀላፊው ባለሃብቶች መሬት አጥሮ ከመቀመጥ አልፈው እንዲያለሙ እንዲሁም ያገኙትን መሬት እና ብድር ለታለመለት ዓላማ እንዲያውሉ አሳስበዋል። ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ባለሃብቱ እና የመሠረተ ልማት ተቋማት ተቀራርቦ በመሥራት ልማቱን እናፋጥናለን ያሉት ቢሮ ኀላፊው ማሽነሪ ላቀረቡ ባለሃብቶች የኃይል አቅርቦት ቅድሚያ እንዲያገኙ፣ ከልማት ባንክ አኳያም የተለየ አበረታች መመሪያ መውጣቱን ጠቅሰዋል።
ኢንዱስትሪ ሰላም ስለሚፈልግ ለሰላም መሥራት ላይ ሁሉም ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተናግረዋል። በመድረኩ ኢንተርፕራይዞች፣ ባለሃብቶች፣ የከተማ እና የክልል መሪዎች እንዲሁም ባለ ድርሻ አካላት ተገኝተዋል። አምራቾችም ምርቶቻቸውን ለሽያጭ እና ለእይታ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
