
ደሴ: ግንቦት 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ደ/ወሎ ዞን መቅደላ ወረዳ የበጋ መስኖ ስንዴ የመስክ ምልከታ ተካሂዷል። አሚኮ ያነጋገራቸው የመቅደላ ወረዳ ጠቢ ክላስተር አርሶአደሮች እንደተናገሩት መንግሥት በቅድመ ዝግጅት ምዕራፉ ባደረገላቸው በቂ የግብዓት አቅርቦት በዚህ ዓመት ውጤታማ የበጋ መስኖ ስንዴ ማልማት ችለዋል።
የደ/ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አቶ አሕመድ ጋሎ በበጀት ዓመቱ ዓመት በዞኑ ከ26ሽ ሄክታር መሬት በላይ በበጋ መስኖ ስንዴ መልማቱን እና ከዚህም ከ7መቶ ሺህ ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኅላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር.) ከቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ የክልሉ መንግሥት ለአርሶ አደሩ ተከታታይ የግብዓት አቅርቦት ድጋፍ ሲደርግ መቆዬቱን በመግለጽ በያዝነው ዓመትም እንደ ክልል ከ153 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በበጋ መስኖ ስንዴ ማልማት መቻሉን እና በዚህም ጥሩ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።
በመስክ ምልከታ መርሐ ግብሩ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋየ፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉን (ዶ.ር) ጨምሮ የክልል እና ዞን መሪዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ: ደምስ አረጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
