
ባሕር ዳር: ግንቦት 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ የሚደረገው ሀገራዊ ምክክር በየጊዜው የሚከሰቱ ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን በዘላቂነት ይፈታል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል። ምክክሩን እንዲመራ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይኽን ትልቅ ኀላፊነት ለመወጣት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መኾኑን የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ በተለይ ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
እንደ ሀገር እጅግ መሠረታዊ በኾኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልዩነቶች ወይም አለመግባባቶችን ለመፍታት የኃይል አማራጭን የመጠቀም ልምድ ይስተዋላል የሚሉት ቃል አቀባዩ የሀገራዊ ምክክሩ ይህን ለዘመናት ኢትዮጵያን ዋጋ ሲያስከፍላት የቆየውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት እና በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ለመፍጠር ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው አብራርተዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመ ከሁለት ዓመት በላይ ያለፈው ሲኾን ባለፉት ጊዜያት እንደ አዲስ የተቋቋመውን መሥሪያ ቤት በሰው ኃይል እና ግብዓት የማደራጀት፣ የምክክርን አስፈላጊነት በተመለከተ ለሕዝቡ ግንዛቤ የመፍጠር፣ አሠራሮችን የመዘርጋት፣ አጋር አካላትን የማፈላለግ፣ የምክክር አጀንዳዎችን የመምረጥ እና ተሳታፊዎችን የመለየት ተግባራት እያከናወነ እንደኾነ ቃል አቀባዩ አስረድተዋል።
የምክክሩ አጀንዳዎች በሦስት መንገዶች እንደሚመረጡም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። ሕዝባዊ መድረኮችን በማመቻቸት፣ ከጥናቶች እንዲኹም ከተለያዩ ተቋማት እና ግለሰቦች በቀጥታ ከሚሰጧቸው ሃሳቦች በመነሳት አጀንዳዎች ይመረጣሉ። አጀንዳ የማሠባሠብ ሂደቱ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ስለመኾኑ የሚናገሩት አቶ ጥበቡ የተለያዩ የፖለቲካ ፖርቲዎች፣ ድርጅቶች እና ሲቪክ ማኅበራት አጀንዳ እያስገቡ ነው። አጀንዳ የማሠባሠብ ሥራው ገና ተሠብሥቦ ያላለቀ ስለኾነ ሕዝቡ በቀጥታ እና በዲጂታል አማራጭ መስጠት ይችላል ብለዋል።
የምክክር ሂደቱን አሳታፊ ለማድረግ ከተለያዩ ተባባሪ አካላት ጋር እየተሠራ እንደኾነ ያነሱት ቃል አቀባዩ በአዋጁ መሠረት የተለያዩ የኀብረተሰብ ተወካዮች፣ የፖለቲካው ማኀበረሰብ እና ልሂቃን በሀገራዊ ምክክር ይሳተፋሉ ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
