
ባሕር ዳር: ግንቦት 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የጎንደር ከተማ አሥተዳደር በከተማ አሥተዳደሩ የዘጠኝ ወራት የመንግሥት ተግባራት አፈጻጸም እና አሁናዊ የከተማዋ የሰላም ሁኔታ ዙሪያ ከከተማ አሥተዳደሩ የመንግሥት ሥራተኞች ጋር መክሯል። ለውይይቱ መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተጽዕኖ እያስከተለ መኾኑን አንስተዋል፡፡ ከዚህ ችግር ለመውጣት ሁሉም ለሰላም ሊሠራ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ በበጀት ዓመቱ ተይዘው የነበሩ የመንገድ፣ የድልድይ እና የተለያዩ የኢንቨስትመንት ልማት ሥራዎች ያሉበት ደረጃ ቀርቦ ውይይት ተደርጎባቸዋል። ከተማ አሥተዳደሩ የመንገድ ተደራሽነትን ለማስፋት የፈጸማቸው የጌጠኛ መንገድ ሥራዎች፣ በችግር ውስጥም ኾኖ ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር የተሠራው ሥራ እና በትምህርት ተቋማት የተማሪ ምገባ መጀመሩ እንዲሁም አዳዲስ ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሠማሩ የተሠራው ሥራ አበረታች መኾኑ ተነስቷል።
በተለይ ስኬታማ መማር ማስተማር እንዲኖር በከተማ አሥተዳደሩ የተማሪዎች ምገባ ሥርአት ለመዘርጋት ታስቦ እስካሁን በ11 ትምህርት ቤቶች የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ምገባ መጀመሩ በውይይቱ ተነስቷል። ስርቆት፣ በእጅ መንሻ ደንበኛን ማስተናገድ እና መሰል ብልሹ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች በከተማዋ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት እንደሚስተዋሉ ተነስቷል። ሕገ ወጥ የቤት ግንባታ መበራከት፣ የሰው ማገት እና መሰል ወንጀሎች መበራከት የውይይቱ ተሳታፊወች ሊቀረፉ ይገባል በሚል ያነሷቸው ጥያቄዎች ናቸው።
አቶ ባዩህ ተወያዮቹ ያነሷቸው ጥያቄዎች ትክክለኛ ችግሮች መኾናቸውን አንስተው ለመፍትሄው እየተሠራ ነው ብለዋል። ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታትም የከንቲባ ችሎት፣ የሥራ አስኪያጆች እና የክፍለ ከተሞች ችሎት ተዘርግቶ የተገልጋዩን ማኅበረሰብ እርካታ ለመጨመር እየተሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
አቶ ባዩህ “ለውጥ እንዲመጣ በለውጥ ሂደት ውስጥ ማለፍ አለብን” በማለት የመንግሥት ሠራተኞች ሙሉ ጊዜአቸውን ለተገልጋዮች እርካታ እና ለከተማዋ እድገት በቅንነት እንዲሠሩ መልክት አስተላልፈዋል። የከተማውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ በሚደረገው ጥረትም ሁሉም ማኅበረሰብ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ የጎንደር ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቻላቸው ዳኘው ናቸው።
ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
