ሕዝቡ ለመንገድ ግንባታ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር መንገድ መምሪያ አስታወቀ።

15

ባሕር ዳር: ግንቦት 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በተያዘው በጀት ዓመት ሕዝቡ ለአዳዲስ መንገዶች ግንባታ እና ጥገና ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር መንገድ መምሪያ አስታውቋል። መምሪያው የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በእንጅባራ ከተማ አካሂዷል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር መንገድ መምሪያ ኀላፊ ጥላሁን ሽቴ በበጀት ዓመቱ የተፈጠረውን ጫና በመቋቋም የሕዝቡን የመንገድ መሠረተ ልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል። ባለፉት 9 ወራት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሦስት ድልድዮች እና 8 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር አዳዲስ የጠጠር መንገዶች ግንባታ መከናወኑን መምሪያ ኀላፊው ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 1 መቶ 50 ኪሎ ሜትር መንገድ በሕዝብ ጉልበት እና በማሽን የታገዘ ጥገና እንደተደረገ የገለጹት መምሪያ ኀላፊው ለዚህም ሕዝቡ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የጉልበት እና የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል ነው ያሉት። በፌዴራል መንግሥት በመገንባት ላይ ካሉት አምስት የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል ሁለቱ በፀጥታ ችግር ምክንያት ሥራቸውን ያቆሙ ሲኾን ቀሪዎቹ ችግሩን ተቋቁመው በሥራ ላይ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

የግምገማው ተሳታፊዎችም ሕዝቡ ሰፊ የመንገድ መሠረተ ልማት ጥያቄዎችን እያነሳ ቢኾንም የፀጥታ እና የበጀት ችግሮች በታቀደው ልክ ምላሽ ለመስጠት እንቅፋት መፍጠራቸውን ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኖራ ለማከም ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
Next articleየጎንደር ከተማ አሥተዳደር የዘጠኝ ወራት የመንግሥት ተግባራት አፈጻጸም እና አሁናዊ የሰላም ሁኔታ ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር መክሯል።