ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኖራ ለማከም ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

30

ባሕር ዳር: ግንቦት 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)አሲዳማነትን በመከላከል እና በኖራ አጠቃቀም ዙሪያ ከደቡብ ጎንደር፣ ምዕራብ ጎጃም፣ ሰሜን ጎጃም እና ከአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከተውጣጡ ባለሙያዎች ጋር ውይይት ተደርጓል። ውይይቱ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎችም የሚካሄድ ይኾናል ተብሏል።

በአማራ ክልል ከሚታረሰው 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በአሲዳማነት መጠቃቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ.ር) ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታሩ በከፍተኛ አሲዳማነት የተጠቃ ነው።

የተሻለ ዝናብ ባለባቸው፣ ምርታማ በኾኑ አካባቢዎች እና ለሀገሪቱ ጭምር ከፍተኛ የምርት ድርሻ ያላቸው የክልሉ አካባቢዎች ይበልጥ የችግሩ ተጋላጭ መኾናቸውን አንስተዋል። በተደጋጋሚ ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ በመዋሉ እና በተደጋጋሚ በመታረሳቸው ምክንያት የአፈር መሸርሸር በማጋጠሙ ይበልጥ ተጋላጭ መኾናቸውን ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት እንደማንኛውም የግብርና ግብዓት ትኩረት ባለመሰጠቱ የአሲዳማ አፈር ልማት ሥራውም ዝቅተኛ እንደነበር ነው የተብራራው። በተያዘው በጀት ዓመት 20 ሺህ 782 ሄክታር መሬት ማከም የሚያስችል 623 ሺህ 550 ኩንታል ኖራ ለማቅረብ የቅድመ ዝግጅት ሥራ አየተሠራ ይገኛል ብለዋል። በ762 ቀበሌዎችም ጥቅም ላይ ይውላል ነው የተባለው።

በዚህም በአሲዳማነት ምክንያት ሊታጣ የሚችለውን 311 ሺህ 775 ኩንታል ምርት ለማዳን ታቅዷል። በተለይም ደግሞ ገብስ፣ ስንዴ እና ባቄላ አምራች አካባቢዎች ማምረት በማቆማቸው እንደ ባሕር ዛፍ በመሳሰሉ ቋሚ ተክሎች እየተተካ ይገኛል ነው የተባለው። በሀገሪቱ ሊታረስ ከሚችለው መሬት ውስጥ 43 በመቶው በአሲዳማነት የተጠቃ ነው። ከዚህም ውስጥ 28 በመቶ በጠንካራ አሲዳማነት ሰለመጠቃቱ ተገልጿል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ብሪክስ የወደፊት ዕጣ ፈንታው ብሩህ ነው” አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
Next articleሕዝቡ ለመንገድ ግንባታ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር መንገድ መምሪያ አስታወቀ።