“ብሪክስ የወደፊት ዕጣ ፈንታው ብሩህ ነው” አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

19

ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ብሪክስ የንግድ እድሎችን በመጨመር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ የቴክኖሎጂ ተደራሽነት እና የውጪ ገበያን ለማብዛት እንደሚረዳ ተገለጸ፡፡ የኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል እና የደቡብ-ደቡብ ትብብርን በማስተዋወቅ ላይ ያላት ሚና፣
ጥቅሞች፣ ተግዳሮቶች እና እድሎች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በውይይቱ ላይ ባቀረቡት የመወያያ ጽሑፍ እንደገለጹት ብሪክስ የደቡብ-ደቡብ ትብብርን በማጠናከር እየተጫወተ ያለው ሚና የሚያበረታታ ነው። ብሪክስ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፋይናንስን ጨምሮ የባሕል እንዲሁም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንደሚፈጥር ጠቅሰው የደቡብ-ደቡብ ትብብር በብሪክስ ሊሻሻል እንደሚችል ገልጸዋል።

ብሪክስ ብዙ ፈተናዎች ቢኖሩትም የወደፊት እጣ ፈንታው ብሩህ ነው ያሉት አምባሳደር ዲና በዓለም ዙሪያ ያሉ ሀገሮች ጥምር ኀይል ተግዳሮቶችን በማሸነፍ የተሻለ ይኾናል ብለዋል። ብሪክስ የንግድ እድሎችን መጨመር፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ የቴክኖሎጂ ተደራሽነት እና የውጪ ገበያን ለማብዛት እንደሚረዳ ገልጸው የግብርና አምራች የኢንዱስትሪ እድገትን የማሳደግ እና የመሠረተ ልማት ግንባታ ድጋፍ እንደሚያስገኝም አስረድተዋል።

ብሪክስ የደቡብ-ደቡብ ትብብርን የሚያበረታታ መኾኑን ጠቅሰው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአፍሪካ ጥብቅና ለመቆም የሚረዳ መኾኑን ጠቁመዋል። ኢፕድ እንደዘገበው በውይይት መድረኩ በኢትዮጵያ የራሺያ አምባሳደር ኢቨገኒ ተረክሂን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ምሁራን ተገኝተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኢንዱስትሪ ፓርኮች የቻይናውያን ባለሃብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየተሠራ እንደኾነ ተገለጸ፡፡
Next articleከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኖራ ለማከም ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ግብርና ቢሮ አስታወቀ።