
ባሕር ዳር: ግንቦት 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በኢንዱስትሪ ፓርኮች የቻይናውያን ባለሃብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን አስታውቋል። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ኮርፖሬሽኑ በሚያሥተዳድራቸው ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን በጠበቁ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ነፃ የንግድ ቀጣና የቻይናውያን ባለሃብቶችን ተሳትፎ በይበልጥ ለማሳደግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
አቶ አክሊሉ ከቻይና ሁናን ግዛት ለመጡ የተለያዩ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ስላሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ዝርዝር ገለጻ አድርገዋል። በመድረኩ ከቻይና ሁናን ግዛት የመጡ እና በአግሮ ፕሮሰሲንግ እና ማዕድን ዘርፍ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ካላቸው የቻይና ባለሃብቶች ጋር ኢንቨስትመንት ተኮር ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱም በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለውን ጠንካራ የኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ እና ለማጠናከር የሚያስችሉ ጉዳዮች አፅንኦት እንደተሰጠባቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስፍሯል። በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት ዋና ሥራ አሥፈፃሚው አክሊሉ ታደሰ ኮርፖሬሽኑ ከዚህ ቀደም ትኩረት ካደረገባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች በተጨማሪ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ ቻይናውያን እና ሌሎችም ባለሃብቶች ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን አሳውቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
