
ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማውን በጎርጎራ ማካሄዱ ይታወሳል። በመድረኩ የፓርቲው ፕሬዚዳንት እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) “ግጭቶችን ማስቀረት ብልጽግናን ማጽናት” በሚል ርእስ ሰፊ ገለፃ አድርገዋል።
በገለጻቸውም የሀሳብ ልዕልና ለማምጣት ፓርቲ ለፓርቲ እና መንግሥት ከሕዝብ የተደረጉ ውይይቶች ሁሉን አሳታፊ የኾነ ሀገራዊ ምክክር እንዲደረግ መሰረት የሚጥሉ እና አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል። መንግሥት ባለፉት ዓመታት በሚሊዮን ከሚቆጠሩ ዜጎች ጋር ውይይቶች ማድረጉን እና ሕዝቡም ለመንግሥት ያለውን ድጋፍ በሰላማዊ ሰልፎች ማረጋገጡን አንስተዋል።
የተከናወኑ የፖለቲካ ሥራዎችም ብልጽግና ፓርቲ እሳቤውን ወደ ሕዝብ ለማስረጽ፣ ከሕዝብ ጋር ለመግባባት እና በሀሳብ ልዕልና ብቻ ለመዳኘት ዕድል መስጠቱን አመልክተዋል። የብልጽግ የፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ የብልጽግና ፓርቲ መሪዎች እና አባላት ከእዳ ወደ ምንዳ በሚል ርእስ ሥልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያን አጠቃላይ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ የፀጥታ እና ደኅንነት ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች መካሄዳቸውን አስታውሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) ከሁሉም ክልሎች ከተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያደረጉት ውይይትም ጠቃሚ ግብዓቶች የተገኙበት እና ፈጣን ምላሽ ለሚሹ ችግሮች መፍትሔ የተሰጡበት መኾኑን ገልጸዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሰማ ጥሩነህ (ዶ.ር) ከሕዝብ ጋር የተደረጉ የውይይት መድረኮች ለቀጣይ ሥራዎች ጠቃሚ ግብዓቶች የተገኙበት መኾኑን ተናግረዋል። የሕግ የበላይነት፣ የኑሮ ውድነት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አሥተዳደር ጉዳይ በሁሉም አካባቢዎች ተመሳሳይ ችግሮች መኾናቸው የጋራ ግንዛቤ መያዙን አንስተዋል።
በመኾኑም ብልጽግና ፓርቲ ከሕዝብ የተነሱት ጥቅል ሃሳቦችን በመያዝ ለመፍትሔው በቁርጠኝነት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ከፓርቲው ግምገማ በመነሳት ሀገራዊ ምክክሩ ወደ ውይይት እንዲሸጋገር እና የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ወደ ትግበራ እንዲገባ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚዎች ተናግረዋል።
በፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ያለውን መልካም ተሞክሮ በማጠናከር እና የአፈጻጸም ጉድለቶችን በማረም ለሕዝብ ቃል የተገቡትን በመተግበር ምላሽ ለመስጠት በቁርጠኝነት ወደ ሥራ መገባቱን አንስተዋል። ኢዜአ እንደዘገበው ልማትን በማስቀጠል ችግሮችን በምክክር በጋራ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ዜጎች ጠንካራ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
