
ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በበጀት ዓመቱ ባለፉት 10 ወራት ከ425 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሠብሠቡን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታውቋል። የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ በሰጡት መግለጫ በበጀት ዓመቱ ባለፉት 10 ወራት 442 ነጥብ 85 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሠብሠብ ታቅዶ 425 ነጥብ 27 ቢሊዮን ብር ተሠብስቧል።
ገቢው ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ54 ነጥብ 77 ቢሊየን ብር እድገት ማሳየቱን ጠቁመዋል። ከተሠበሠበው አጠቃላይ ገቢ 271 ነጥብ 36 ቢሊዮን ብር በላይ የሚኾነው ከሀገር ውስጥ ግብር ከፋዮች የተሠበሠበ ነው፡፡ ቀሪው 153 ነጥብ 91 ቢሊዮን ብር ደግሞ ከውጭ ንግድ ቀረጥ እና ታክስ የተሠበሠበ መኾኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
እንደ ወይዘሮ አይናለም ገለጻ በሚያዝያ ወር 51 ነጥብ 51 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ ታቅዶ 51 ነጥብ 07 ቢሊየን ብር ተሠብስቧል። ሚኒስትሯ የሀገሪቱን የግብር ሥርዓት ለማዘመን በዲጂታላይዜሽን ሥራዎች ላይ ትኩረት መደረጉን አስረድተዋል።
ቀረጥ እና ታክስ የመክፈል ባሕል ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ቢያሳይም አሁንም ተጨማሪ ሥራዎች መሥራት እንደሚያስፈልግ የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
