የፍኖተ ካርታው ዝግጅት በሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ወደ ትግበራ እንደሚገባ የፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ።

19

ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማስተግበሪያ ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ መኾኑን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ በአዲስ አበባ እና በሁሉም ክልሎች በሚገኙ ከተሞች ከ80 በላይ የግብዓት ማሰባሰቢያ የምክክር መድረኮች ተካሂደዋል፡፡ በእነዚህ መድረኮች የተገኙ ሃሳቦችን መሰረት በማድረግ በገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን የተዘጋጀው ረቂቅ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወሳል፡፡

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የተመላከቱ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በመፈጸም ረገድ የትግበራ ምዕራፉ መቼ እና እንዴት ተጀምሮ ተፈጻሚነቱ የሚያበቃበትን ሁኔታ ለማመላከት የፍኖተ ካርታ ወይም ዝርዝር የድርጊት መርሐ ግብር ማዘጋጀት አስፈላጊ መኾኑ ተጠቅሷል፡፡ በዚህ መሰረትም ይህንን በተለያዩ ጊዜያት በሀገሪቱ በተፈጸሙ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች የተፈጠሩ ቁስሎችን በተለያዩ የሽግግር ፍትሕ ስልቶች አማካኝነት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት መስጠት የሚያስችል ማስፈጸሚያ ፍኖተ ካርታ በመዘጋጀት ላይ መኾኑ ተገልጿል፡፡

ፍኖተ ካርታው ዘላቂ ሰላምን፣ የሕግ የበላይነትን፣ ፍትሕን እና የሰብዓዊ መብትን ለማረጋገጥ የተቀመጠውን የፖሊሲ አቅጣጫ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያስችም ተጠቅሷል፡፡ የፍኖተ ካርታው ዝግጅት ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና ከሲቪል ማኅበረሰብ ብሔራዊ አደረጃጀቶች የተውጣጡ ከፍተኛ ባለሙያዎችን በያዘ ቡድን እየተከናወነ መኾኑ ነው የተገለጸው፡፡

ፍኖተ ካርታው የፖሊሲ ትግበራ ምዕራፉ የሚያልፍባቸውን ሂደቶች በዝርዝር ከማመላከት በተጨማሪ በፖሊሲው ትግበራ የባለድርሻ አካላትን ሚና፣ የመፈጸሚያ የጊዜ ወሰንን እና ሥራው የሚጠይቀውን የበጀት መጠን ያመላክታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የፍኖተ ካርታው ዝግጅት በሶስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ወደ ትግበራ የሚገባ መኾኑን ከፍትሕ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በእምቦጭ የተወረረ፤ በታሪክ የከበረ ሐይቅ”
Next articleባለፉት 10 ወራት ከ425 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሠበሠበ፡፡