“በእምቦጭ የተወረረ፤ በታሪክ የከበረ ሐይቅ”

54

ባሕር ዳር: ግንቦት 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)አያሌ ገዳማት እና አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙበት፣ ቅዱሳን አበው እና እመው መንነው የሚኖሩበት፣ አምላክ ለሀገር ፍቅርን፣ ሰላምን እንዲሰጣት፣ ገበያውን እንዲያጠግብላት፣ ሕዝቦቿን በረሃብ እንዳይቀጣባት፣ ጠብና ጥላቻን እንዲያርቅላት፣ አንድነቷን እንዲያጸናላት፣ ጠላቶቿን ፈጥኖ እንዲያስገዛላት፣ ዳሩን እሳት፣ መሀሏንም ገነት አድርጎ እንዲያኖራት ያለማቋረጥ ይማጸኑበታል።

የኢትዮጵያን ታላቅነት፣ ጥንታዊት እና ቀደምትነት ይነግሩበታል። ታሪክ የሚነገርበት፣ ምስጢር የሚመሰጠርበት፣ ታላቅነት የሚታይበት እና ጥበብ የሚኖርበት ነው። ነገሥታቱ ካባቸውን ጥለው፣ መጫሚያቸውን አውልቀው፣ ከዙፋን ወርደው፣ እንደመነኮሳት በባዕት ተወስነው ሱባዔ ገብተውበታል። ሀገራቸውን እንዲባርክላቸው፣ ዘመናቸውን እንዲያሳምርላቸው፣ ዘመናቸው ባለፈ ጊዜም ነፍሳቸውን እንዲቀበልላቸው ተማጽነውበታል። ያማሩ አብያተክርስቲያናትን አሳንጸውበታል፣ የተዋቡ ገዳማትን ገድመውበታል።

በዚህ ሐይቅ የቅዱሳን እና የነገሥታቱ አጽም በክብር አርፎበታል፣ ቅርሶች በክብር ተቀምጠውበታል። የዓለማውያን ዐይን ያልተመለከተው፣ የዓለማውያን አዕምሮ ያልመረመረው፣ ለመርመርም የማይቻለው ምስጢር መልቶበታል። ታዲያ ይህንን ታላቅ እና ታሪካዊ ሐይቅ እምቦጭ የሚሉት ጠላት ተነስቶበታል። ዙሪያውን እየወረረ ሕልውናውን ተፈታትኖታል፡፡ እምቦጭን ለማጥፋት እና የከበረውን ሐይቅ ከጥፋት ለመታደግ ለዓመታት ተሠርቷል። ማጥፋት ባይቻልም መቀነስ የተቻለባቸው ዓመታት ነበሩ። ዘንድሮ ግን ይህ አልኾነም። የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ለጣና ደራሽ እንዲጠፋ አድርጎታል። በዚህም ሳቢያ እምቦጭ ጣናን እየጎዳው ነው፡፡

ሐምሌ 2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ እስካሁን ድረስ የእምቦጭ አረም በስፋት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የመከላከል ሥራ አልተሠራም። እያየኝ ብርሃኔ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጣና ሐይቅ እና ሌሎች ውኃማ አካላት ጥበቃ እና ልማት ቡድን መሪ ናቸው። በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በአራት ወረዳዎች በ21 ቀበሌዎች የእምቦጭ አረም አለ ይላሉ። ከዚህ ቀደም በኅብረተሰብ ተሳትፎ የእምቦጭ አረም የመከላከል ሥራ ይሠራ ነበር። በዚህ ዓመት ግን ምንም ዓይነት ሥራ ባለመሠራቱ አረሙ እየሰፋ እና እየጨመረ ሄዷል ነው ያሉት።

የፀጥታ ችግሩ በንቅናቄ ለመሥራት አልተቻለም፤ አረሙ እንዲጨመር አድርጎታል። ባለሙያዎችን ልኮ አካባቢ በውል ለመለየት ባለመቻሉ እየጨመረ እና እየሰፋ መሄዱን ግልፅ ነው ይላሉ። እምቦጭ ውኃ መጣጭ አረም በመኾኑ ጣና አደጋ ውስጥ ይወድቃል ነው ያሉት። በእምቦጭ አረም ምክንያት በጣና ሐይቅ ላይ የሚገኙ ጥቅሞች ሁሉ እየቀነሱ ይሄዳሉ ይላሉ። በፀጥታ ችግሩ ምክንያት እምቦጭን አለመከላከል ብቻ አይደለም፣ ማሽኖችን ለመጠበቅም ተቸግረናል፣ ማሽኖች አደጋ ላይ ናቸው፣ ስርቆት እየተፈጸመባቸው ነው ብለዋል። ለጣና ሐይቅ ልዩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፣ መንግሥት ልዩ ድጋፍ በማድረግ እምቦጭን መከላከል አለበት፤ ረጂ ደርጅቶችም ታች ድረስ እየወረዱ ድጋፍ ቢያደርጉ ሕልውናውን መታደግ ይቻላል ነው ያሉት።

ጣና ሐይቅ ዘላቂ ሃብት ነው፣ ጣና የእኛ ሃብት ነው ብሎ ማመን ይገባል፣ ጣናን እንደ ፖለቲካ ማየት ካለ ችግር ነው፣ ከፖለቲካ በላይ ነው፣ ትልቁ የቱሪስት መስህብ ነው ይላሉ። ሰላምን ማጽናት እና ትኩረታችንን ጣና ላይ ማድረግ አለብን ብለዋል። አቶ ማሙሽ ንጉሤ ደግሞ የደቡብ ጎንደር ዞን የጣና ሐይቅ እና ሌሎች ውኃማ አካላት ጥበቃ ልማት ቡድን መሪ ናቸው። በዞኑ በሦስት ወረዳዎች የእምቦጭ አረም መከሰቱን ገልጸዋል። ባለፉት ዓመታት በተሠሩ ተከታታይ ሥራዎች እምቦጭ ከአቅም በላይ የማይኾንበት ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር አንስተዋል። በዚህ ዓመት በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ መሠራት የሚገባቸው ሥራዎች ባለመሠራታቸው እምቦጭን መከላከል አልተቻለም ነው ያሉት። ክረምቱ እንዳበቃ ምን ያክል የእምቦጭ አረም እንዳለ በቴክኒክ ሙያተኞች አማካኝነት በቴክኖሎጂ በመታገዝ ይታወቅ እንደነበር የተናገሩት አቶ ማሙሽ ዘንድሮ ግን ይሄንም ማድረግ ሳይቻል መቅረቱን ነው የተናገሩት።

አረሙ መስፋፋቱ ቀጥሏል ነው ያሉት። ባለሙያዎች ኅብረተሰብን አስተባብረው ለመሥራት አልቻሉም፤ እንኳን ሥራ ሳይሠራ የመከላከል ሥራ እየተሠራ እንኳን እምቦጭን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት አልተቻለም። ጊዜ ባገኘ ቁጥር ሐይቁን እና አካባቢውን ለከፍተኛ አደጋ ያጋልጣል፣ የአንድ ዓመት ሥራ ባልሠራን ቁጥር የአራት ዓመታት ሥራ ይጠብቀናል ይላሉ። እኛ ምንም ዓይነት ሥራ አልሠራንም፣ እምቦጭ ግን የራሱን ሥራ እየሠራ ነው፤ ይሄም ለሐይቁ አደጋ ነው ብለዋል።

አርሶ አደሮች በራሳቸው መሬት እና አዋሳኝ ያለውን አምቦጭ እንዲከላከሉ ጥረት እያደረግን ነው፣ ነገር ግን ውጤታማ አይደለም ይላሉ። ጣና የጋራ ሃብት በመኾኑ፣ በጋራ ተነጋግሮ፣ በአካባቢው ያለውን ስጋትን ቀንሶ መሥራት ይገባል፣ ያ ካልኾነ ማኅበረሰቡ የመኖር እና ያለመኖር ጉዳይ ውስጥ ስለገባ የአካባቢውን ሰላም በማረጋገጥ መረባረብ ይገባል ብለዋል።

የጣና ሐይቅ እና ሌሎች ውኃማ አካላት ጥበቃ እና ልማት ኤጄንሲ በፀጥታ ሁኔታው ሥራ መሥራት አልቻልንም ብሏል። ቀደም ሲል በማኅበረሰብ ንቅናቄ እና በማሽን አረሙን የመከላከል ሥራ ይሠራ ነበር አሁን ግን ይሄን ማድረግ አልተቻለም ነው ያለው። በፀጥታው ምክንያት የእምቦጩን ስፋት በትክክል ለማወቅ አለመቻሉንም አመላክቷል። እምቦጭም እየተስፋፋ መኾኑን ገልጿል።

ኤጄንሲው እምቦጭ በሐይቁ ላይ ጉዳት በማያደርስበት ሁኔታ ላይ የማድረስ ሥራ ሠርቶ እንደነበርም አመላክቷል። የፀጥታ ችግሩ ግን እምቦጭ እንዲስፋፋ እድል ሰጥቷል ነው ያለው። ሁሉም ለጣና ሐይቅ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸውም አሳስቧል። ሐይቁን ለመታደግ የፀጥታው ጉዳይ አስተማማኝ መኾን አለበት ብሏል። ማኅበረሰቡም ልዩ ትኩረት ማድረግ አለበት ነው ያለው። በሐይቁ ዳርቻ ላይ ያለውን ወሰን አለመከለልም የሐይቁን ጥበቃ አስቸጋሪ እንዳደረገው አንስቷል። ሐይቁ በሸሸ ቁጥር እየተከተሉ ማረስ አልቀረም ነው የተባለው።

በባሕር ዳር ከተማ ዙሪያ የእምቦጭ አረም መከሰቱንም ኤጄንሲው አስታውቀዋል። በከተማዋ ዙሪያ የተከሰተውን እምቦጭ አረም ስጋት ሳይኾን ለመከላከል እየተሠራ መኾኑንም ገልጿል። ማኅበረሰቡ እና ማኅበራት አዲስ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለመከላከል ያሳዩት ንቅናቄ የሚደነቅ መኾኑንም አስታውቋል። ሰላምን በማረጋገጥ የጣናን ሕልውና መጠበቅ እንደሚገባም አስገንዝቧል።

ታሪክ እና ብዝሃ ሕይዎት የጸናበት ሐይቅ አደጋው ሳይሰፋበት፣ ችግሩ ከዚህም ብሶ ሳይጠነክርበት ኢትዮጵያዊ ሁሉ ትኩረት ሊያደርግበት ግድ ይለዋል። ለምን ካሉ የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያን ውድ እና ልዩ ሃብት ነውና።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” በሚል መሪ መልዕክት የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት የንቅናቄ መድረክ በባሕር ዳር ተጀመረ።
Next articleየፍኖተ ካርታው ዝግጅት በሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ወደ ትግበራ እንደሚገባ የፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ።