“293 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሕጋዊነታቸው እንዲሰረዝ ውሳኔ ተሰጥቷል” የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን

23

ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአዲሱ አዋጅ ድጋሚ ያልተመዘገቡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ሕጋዊነት ሊሰረዝ መኾኑን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ገልጿል። ባለሥልጣኑ ሪፖርት ያላደረጉ 293 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንዲሰረዙ በቦርድ መወሰኑን ገልጿል።

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ በቀድሞው አዋጅ መሠረት ተመዝግበው ነገር ግን በአዲሱ አዋጅ ደግሞ ድጋሚ ያልተመዘገቡ 1 ሺህ 554 የሲቪል ማኅበራት ህልውናቸውን እንዲያጡ ተወስኗል ብለዋል፡፡ ዳግም እንዲመዘገቡ ከሚጠበቁት ድርጅቶች መካከል 2ሺህ የሚኾኑት ግዴታቸውን የተወጡ ሲኾን 1 ሺህ 554 የድጋሚ ምዝገባውን አላከናወኑም ብለዋል።

የሲቪክ ማኅበራትን የማስፋፋት ዓላማ በመያዝ በድጋሚ እንዲመዘገቡ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል። በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መልዕክት መተላለፉንና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመዋል። ሕጋዊነታቸውን ሳያረጋግጡ ስም ይዘው ብቻ መቀጠል ስለማይቻል ድጋሚ ምዝገባ ያላከናወኑ ድርጅቶች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ከሐምሌ አንድ ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ይኾናል ሲሉ አስረድተዋል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ በሦስት መንገዶች ክትትል ያደረጋል፡፡ ድርጅቶቹ በየዓመቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴያቸውን የሚጠቁም ሪፖርት እንዲያቀርቡ በማድረግ፣ የመስክ ምልከታ በማከናወን እንዲሁም ድርጅቶቹ የሕዝብ እንደመኾናቸው የተለያዩ ጥቆማዎችን በመቀበል ክትትል እንደሚደረግባቸው አብራርተዋል፡፡

ባለሥልጣኑ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ በሚያደርገው ክትትል 293 ድርጅቶች ሪፖርት የማድረግ ግዴታቸውን እንዳልተወጡ መረጋገጡን አመላክተዋል። ሪፖርት ማድረግ የድርጅቱ ህልውና ስለመኖሩ አንድ ማረጋገጫ ነው ያሉት አቶ ፋሲካው ሪፖርት ያላደረጉ ድርጅቶች ስማቸውን በጋዜጣ በማውጣት ጥሪ መደረጉንም ገልጸዋል።

ምናልባት ያልሰሙ ድርጅቶች ወይም የገንዘብ ችግር ገጥሟቸው የዘገዩ ድርጅቶች ካሉ በሚል ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የአንድ ዓመት የጊዜ ገደብ በመስጠት ሲጠብቅ ቆይቷል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ የተሰጠው ገደብ እስከ ሚያዚያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም እንደነበር አስታውሰው እስካሁን ሪፖርት ባለመደረጉ ቦርዱ ሚያዚያ 30 ባደረገው ሥብሠባ 293 ድርጅቶች ሕጋዊነታቸው እንዲሰረዝ ውሳኔ ማስተላለፉን አስታውቀዋል።

አንድ ድርጅት ሲፈርስ የነበረው ሃብት ተመርምሮ እንደሚጣራ የተናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በተላለፈው ውሳኔ መሠረት ከሐምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ያላቸውን ሃብት የማጣራት ሥራው ይጀመራል ብለዋል። ኢፕድ እንደዘገበው እንዲሰረዙ ውሳኔ የተላለፈባቸው ድርጅቶች እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ አሳማኝ ምክንያት ማቅረብ ከቻሉ ከስረዛው ነጻ የሚኾኑበትን መንገድ ማመቻቸቱንም አቶ ፋሲካው አመላክተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጦርነት አውዳሚና ችግር አባባሽ መኾኑን ተገንዝበን ሁላችንም ለሃሳብ ልዕልና ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን” አረጋዊ በርሄ (ዶ.ር)
Next article”ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” በሚል መሪ መልዕክት የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት የንቅናቄ መድረክ በባሕር ዳር ተጀመረ።