
ባሕር ዳር: ግንቦት 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጦርነት ችግር ፈቺ ሳይኾን አውዳሚ እና ቀውስ አባባሽ መኾኑን ተገንዝበን ሁላችንም ዘመኑ ለሚጠይቀው እና አትራፊ ለኾነው የሃሳብ ልዕልና ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን ሲሉ የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር አረጋዊ በርሄ (ዶ.ር) ተናግረዋል፡፡
ዶክተር አረጋዊ በርሄ ጦርነት ችግርን ከማባባስ ልዩነቶችን ከማስፋት በቀር የትኛውንም ችግር ፈትቶ አያውቅም ብለዋል፡፡ አሁን ላይ ሁሉም ሊከተለው የሚገባው እና ዘመኑ የሚጠይቀው የተሻለ ሃሳብን ይዞ ወደ ውይይት መምጣት እንደኾነም አስገንዝበዋል፡፡ በዚህ ዘመን ቁረጠው፣ ፍለጠው እና ግጠመው ሳይኾን የሚያስፈልገን የሃሳብ ልዕልና የሚስተዋልበት ለሀገር እና ለወገን የሚጠቅም የበሰለ ሃሳብ ማምጣት ነው ብለዋል፡፡ ዶክተር አረጋዊ ልሂቃን ዳር ቆመው ጦርነቱ እኛን እስካልነካን ድረስ ማለታቸውን ትተው ሕዝቡን በማሳመን እና የውይይት መንፈስን በማስረጽ በኩል የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡
እስከ አሁን የተደረጉት ጦርነቶች በሙሉ ያሳዩን ነገር ቢኖር ጥፋትን፣ ውድመትን፣ ውድቀትን እና ኋላ ቀርነትን ነው ያሉት ዶክተር አረጋዊ ልዩነት መሠረታዊ እና የሚጠበቅ ነገር ከመኾኑም በላይ እንኳን የእኛን ያህል ሰፊና ብዙ ሕዝብ ያለባት ሀገር ይቅር እና ትንሽ ሕዝብ የያዙ ሀገሮችም በውስጣቸው ሰፋፊ ልዩነቶች አሏቸው ነው ያሉት፡፡ ልዩነቶችን ሁሉ በጦርነት እንፈታለን፤ በግጭት መልስ እናገኛለን ማለት አግባብነት የሌለው ተግባር መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
በግጭት የሚመጣ ለውጥ ወይም እድገት እንደሌለ ገልጸው የጦርነት ጦሱ ወገንን ማጣት፣ ሀገርን ባዶ ማድረግ፣ ኢኮኖሚን ማድቀቅ፣ ሃብትን ማባከን፣ ለዓመታት የተደከመባቸውን መሠረተ ልማቶች አውድሞ በብዙ ዓመታት ወደ ኋላ መመለስ እንደኾነ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ደግሞ የመጣንበት ሂደት ራሱ የሚያሳየን በመኾኑ ከዚህ ለመውጣት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
እንደ ኢፕድ ዘገባ “እኛ የአንድ እናት ልጆች አንድ የኾንን ሕዝቦች ነን፤ ያሉብንን ችግሮች እና ልዩነቶች በሰከነ መንገድ በውይይት የተሻለ ሃሳብን በማፍለቅ ልንፈታ ይገባል” ያሉት ዶክተር አረጋዊ መንግሥትም ችግሮችን ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ከማለፍ ይልቅ የቱ ጋር ነው ስህተቱ የሚለውን እየመረመረ መፍትሔ ማስቀመጥ እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
