
ባሕር ዳር: ግንቦት 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በዓለማችን በጣም ፈጣን የሚባለውን ለውጥ እያስመዘገበ የሚገኘው ዲጀታል ቴክኖሎጂ የሰው ልጅ ባለው መስተጋብር እና አጠቃቀም ሁለት መልክ ይዟል። ለመልካም ተብሎ የሚፈጠር ነገር እንዳለ ሁሉ በተመሳሳይ ለጥፋትም ይውላል። የሰውን ልጅ እንዲያግዝ የሚፈጠረው ቴክኖሎጂ የሰው ልጅ መጥፊያም ሲኾን ይስተዋላል። የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች መነሻቸው በጎ ዓላማ የሰነቁ ቢኾንም በሰው ልጅ የትግበራ ልዩነት ለጥፋት ዓላማም ሲውሉ ደግመን ደጋግመን አስተውለናል።
በመሠረታዊነት ግን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ከሰው ልጆች ችግር የሚፈልቁ በመኾናቸው እና ተቀባይነታቸውም የሚረጋገጥላቸው በሚያበረክቷቸው በጎ አስተዋጽኦዎች በመኾኑ ለመልካም ተግባር ታልመው የሚፈጠሩ ናቸው። የሰው ልጅ በተለያየ አጋጣሚ በዲጂታል የማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚያገራቸው የጽሑፍ፣ የፎቶ እና የቪዲዮ ይዘቶች ዘመን የወለዳቸውን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ሳቢ እና ተወዳጅ እንዲኾኑ ማድረግ ይቻላል። ፎቶ ግራፎች እና ቪዲዮዎች ላይ የተለያዩ ውበት ፈጣሪ ልውጠቶችን በመጠቀም የጥራት ደረጃቸውን ከፍ ለማድረግ የፎቶ እና ቪዲዮ ኤዲቲንግ መተግበሪያዎች አገልግሎት ላይ ይውላሉ።
በሌላ መልኩ ደግሞ ምስሎች ላይ ሌላ ተጨማሪ ይዘት በመጨመር የሃሰት መረጃ ለማስተላለፍ፣ ለማጭበርበር፣ የሰውን ዝና እና ክብር ለማጉደፍ ቴክኖሎጂ ያመጣቸው መገልገያዎች አገልግሎት ላይ ሲውሉ መመልከት አዲስ ነገር አይደለም። በማኅበራዊ ትስስር ገጾች በቀላሉ ሰዎችን ለማሳሳት ጥቅም ላይ ከሚውሉ ይዘቶች ውስጥ ፎቶግራፍ የመጀመሪያው ነው። ትክክለኛው ፎቶ ላይ ጊዜን፣ ቦታን እና ሁኔታን የሚያመላከቱ የምስል መግለጫዎችን በመቀየር የማሳሳት እና የማጭበርበር ተግባራት ይፈፀማሉ።
የፎቶግራፎችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ምስሉ ከዚህ በፊት ጥቅም ላይ መዋል አለመዋሉን፣ ምስሉ ላይ የተለየ ነገር መኖር አለመኖሩን፣ ምልክት የሚኾን የምናውቀው ነገር መኖሩን እና አካባቢው ምን እንደሚመስል በጥልቀት መመርመር ያስፈልጋል። የቴክኖሎጂ መዘመን በምስሎች የሚፈፀም ማጭበርበርን ውስብስብ እያደረገው በመምጣቱ ምስሎችን በዐይናችን ብቻ በመመልከት በጥልቀት መርምረን ለመረዳት እና ለመለየት አዳጋች ኾኗል።
አጋዥ የመስመር እና ከመስመር ውጭ የኾኑ መተግበሪያዎችን በመጠቀም የተጭበረበሩ ምስሎችን በጥልቀት እና በጥራት የምንለይባቸው መንገዶች መኖራቸው ደግሞ መልካም ነገር ነው። ብዙ ዓይነት ምስሎችን የምናጣራባቸው መንገዶች ቢኖሩም የተለመዱ እና ለአጠቃቀም ቀላል ከኾኑት ውስጥ ጉግል ሪቨርስ ኢሚጅ ሰርች፣ ቲን አይ እና ፎቶ ፎሬንሲክ ተጠቃሽ ናቸው።
ጉግል ሪቨርስ ኢሚጅ ሰርች:- ለማረጋገጥ ያስገባንለትን ምስል እጅግ ብዙ ከኾኑ የሳይበር ዓለም ምስሎች ጋር በማነፃፀር ተያያዥ፣ የተቀየጡ እና ራሱን ያስገባነውን ምስል ጨምሮ ያመጣልናል። ምስሉን ለመፈለግ ነጥቦችን፣ መስመሮችን፣ ቀለሞችን እና ቴክስቼሮችን በጥልቀት ያጤናል። ቲን አይ ደግሞ እንዲፈለግ የተሰጠውን ምስል በመጀመሪያ መለያ ይፈጥርለት እና ለዚያ መለያ የሚገጥም ሌላ ምስል ይፈልጋል። የፍለጋ ውጤቱ ራሱን የተፈለገውን ምስል፣ በዋናው ምስል ላይ ለውጥ ከተደረገ ያን የተለወጠ ምስል እና ከዋናው ምስል ላይ የመጠን ለውጥ ተደርጎበት ከኾነም ያንኑ ያመጣልናል።
ፎቶ ፎሬንሲክ የሰው ዐይን ሊያስተውለው የማይችለውን ይዘት በጥልቅ ምልከታ በመመርመር ለመለየት ያስችላል። በተለየ ሁኔታ ምስሉ የተቀረፀበትን መሳሪያ ሞዴል፣ ቦታ እና የተጨመረ ቅንብር ይለያል። የቴክኖሎጂ እድገት እና የመረጃ ተለዋዋጭነት ካለው ፍጥነት አንፃር በሳይበር ዓለም የምናገኘውን ይዘቶች ትክክለኛነት ማረጋገጥ ጠቀሜታው ጉልህ ነው።
smartframe.io እና help.tineye.com የመረጃ ምንጮቻችን ናቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
