ኮሚሽኑ የሒሳብ ኦዲት ግኝቱን በማስተካከል እስከ ግንቦት 30 ሪፖርት እንዲያደርግ ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ።

18

ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴራል ሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በ2014 በጀት ዓመት የሒሳብ ኦዲት ግኝቱን በማስተካከል እስከ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ለሚመለከታቸው አካላት ሪፖርት ማድረግ እንዳለበት በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳስቧል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ይህንን ማሳሰቢያ የሰጠው የፌዴራል ሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በ2014 በጀት ዓመት የተለዩ የሂሳብ ግኝቶችን አስመለክቶ የመንግሥት ወጪ፣ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፤ ከፌዴራል ዋና ኦዲተር፣ ከፌዴራል ሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የሥራ ኀላፊዎች ጋር በተወያየበት ወቅት ነው፡፡

የመንግሥት ወጪ፣ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሺእመቤት ደምሴ (ዶ.ር) ኮሚሽኑ በ2014 በጀት ዓመት የሒሳብ ኦዲት ግኝቱን ለማስተካከል የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል። ከኦዲት ግኝቱ በኋላ ኮሚሽኑ በንብረት አያያዝ ያደረገውን ማስተካከያ አጠናክሮ በማስቀጠል ለሌሎች መሥሪያ ቤቶች አርዓያ መኾን አለበት ነው ያሉት፡፡

ዶክተር የሺእመቤት በፌዴራል ዋና ኦዲትር የኮሚሽኑ የአሠራር ክፍተቶች ናቸው ተብለው የተለዩ የሒሳብ ኦዲት ግኝቶችን ለማስተካከል መርሐ ግብር አዘጋጅቶ በመሥራት የወሰደውን ማስተካከያ ለመንግሥት ወጪ፣ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ኮሚሽኑን ለሚከታተለው የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ለፌዴራል ዋና ኦዲተር እና ለገንዘብ ሚኒስቴር እስከ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ሪፖርት ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

በፌዴራል ዋና ኦዲተር የተለዩ የአሠራር ክፍተቶችን ለማረም ኮሚሽኑ እቅድ ሲያቅድ በእያንዳንዱ የሒሳብ ርእስ መሠረት ማቀድ እንዳለበት ጠቁመዋል። ተሰብሳቢ እና ተከፋይ ሒሳቦችን አስመልክቶ የተለዩ ጉዳዮችም እልባት ሊሰጣቸው እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡ የሁለቱ ቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው ኮሚሽኑ የኦዲት ግኝቱን ለማስተካከል እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ሌሎች መሥሪያ ቤቶች በአሠራር ግድፈት ወደ ሙስና እና ብልሹ አሠራር እንዳይገቡ ኮሚሽኑ የሚቆጣጠር በመኾኑ የአሠራር ክፍተቶችን በማስተካል ለሌሎች መሥሪያ ቤቶች አርዓያ መኾን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ የሒሳብ አሠራሮችን በቴክኖሎጂ በመደገፍ በፌዴራል ዋና ኦዲተር የተለዩ አሠራር ክፍተቶችን ማረም እንዲቻል ኮሚሽኑ ሒሳብ ወጪ እና ገቢን እንዲሁም ግዥን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ሕግ እና የአሠራር ሥርዓትን ተከትሎ በመሥራት ከችግር መውጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲትር መሠረት ዳምጤ በፌዴራል ዋና ኦዲተር ከተለዩ የአሠራር ክፍተቶች አንዱ ትክክለኛ የሂሳብ ርእስን እና መደብን ተከትሎ አለመሥራት መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ ኮሚሽኑ የግዥ ሕጎችን እና የአሠራር ሥርዓቶችን ተከትሎ በመሥራት ከችግር መውጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ዋና ኦዲተሯ አያይዘውም ተሰብሳቢ ሒሳብን በወቅቱ አለመሰብሰብ የመሰብሰብ እድሉን ስለሚያጠበው እና ተከፋይ ሒሳብን በወቅቱ አለመክፈልም በመንግሥት ላይ ጫና ስለሚፈጥር በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የፌዴራል ሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነሮች እሸቴ አስፋው እና አቶ ወዶ አጦ የተሰጡት አስተያየቶች ጠቃሚ በመኾናቸው ኮሚሽኑ የእቅዱ አካል አድርጎ እንደሚጠቀምባቸው መግለጻቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያሳያል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበቀጣናው ”የኢንቨስትመንት እምብርት” ተብሎ ከሚጠራው ነጻ የኢኮኖሚክ ዞን ጠንካራ ተሞክሮዎች መወሰዳቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
Next articleምሥል ማጣሪያ መንገዶች