
ባሕር ዳር: ግንቦት 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአዘርባጃን መንግሥት የኢኮኖሚ ፕሮግራሞች ውስጥ አንዱና ዋና የኾነውን ‘አላት’ የተሰኘውን ነጻ የኢኮኖሚክ ዞን ስለመጎብኘታቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ ገልጸዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘አላት’ ነጻ የኢኮኖሚክ ዞን ተኪ ምርቶች እና ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች በጥራት እና በስፋት የሚዘጋጁበት ስፍራ ስለመኾኑ ነው የገለጹት።
በኢኮኖሚክ ዞኑ ለአምራቾች ኢንዱስትሪ ባለሃብቶች ጥሩ የሥራ ከባቢን በመፍጠር፣ ዕውቀት መር በኾነ መንገድ እሴትን ጨምሮ ማምረት እና ፈጠራ የታከለባቸው ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርቶችን በጥራት በማምረት ተወዳዳሪ ኾነው ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ ስለማድረጋቸውም መገንዘባቸውን ተናግረዋል፡፡
ከአዘርባጃን አልፎ የቀጣናው ”የኢንቨስትመንት እምብርት” ተብሎ ከሚጠራው ነጻ የኢኮኖሚክ ዞን ጠንካራ ተሞክሮዎችን ስለመወሰዳቸውም ነው ያብራሩት።
በስፍራው ስለተደረገላቸው አቀባበል እና ገለጻ የኢኮኖሚክ ዞኑን ሊቀ መንበር ቫለህ አላስግሮቭ እና የሥራ ባልደረቦቻቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን አመሥግነዋል፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ እንዳሉት ግንኙነትን በማጠናከር እና ምርጥ ልምዶችን በመቀመር ኢትዮጵያ በዘርፉ የሚጠበቅባትን ለመፈፀም ተገቢውን ክትትል ታደርጋለች ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
