የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ምርቶች አውደ ርዕይ በደቡብ ሱዳን ተከፈተ፡፡

32

ባሕር ዳር: ግንቦት 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ምርቶች አውደ ርዕይ በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ እየተካሄደ ነው፡፡ በአውደ ርዕዩ ላይ 16 የኢትዮጵያ ኩባንያዎች የኢንዱስትሪ ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅ ላይ ናቸው ተብሏል፡፡ አውደ ርዕዩ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ አቅም ማሳየት እና ከደቡብ ሱዳን ጋር የተሻለ እና ዘላቂ ምጣኔ ሃብታዊ ትብብር እና የኢንቨስትመንት ትስስር ማጎልበት ላይ ያለመ ነው፡፡

በአውደ ርዕዩ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ የኢንቨስትመንት ሚኒስትር ዲኢዩ ማቶክ ዲንግ ዎል (ዶ.ር) የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች በደቡብ ሱዳን ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎችን አሟጠው እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል። ዶክተር ዎል የሁለቱን ሀገራት ገበያ ማስተሳሰር ለጋራ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት እና ብልጽግና ወሳኝ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።

በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ነቢል ማህዲ በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን መካከል ያለውን የመሠረተ ልማት ትስስር በማጠናከር የንግድ እና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን ማቀላጠፍ እንዲሁም ቀጣናዊ ልማትን ማጎልበት እንደሚስፈልግ ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳሰፈረው የኢትዮጵያ እና የደቡብ ሱዳን የንግድ እና ኢንቨስትመንት አውደ ጥናትም እየተካሄደ ይገኛል።

መድረኩን የከፈቱት የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የመሠረተ ልማት ክላስተር ሊቀመንበር ጄኔራል ታባን ዴንግ ጋይ አውደ ጥናቱ በኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን መካከል ጥልቅ ትብብርን እንደሚያጎለብት፣ ምጣኔ ሃብታዊ ትስስርን እንደሚያጠናክር እና ጠቃሚ የትብብር እድሎችን እንደሚከፍት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅትን የምትቀላቀልበትን ሂደት ማፋጠን በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ውይይት ተካሄደ።
Next articleበቀጣናው ”የኢንቨስትመንት እምብርት” ተብሎ ከሚጠራው ነጻ የኢኮኖሚክ ዞን ጠንካራ ተሞክሮዎች መወሰዳቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡