
ባሕር ዳር: ግንቦት 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የዓለም የንግድ ድርጅት የአዲስ አባል ሀገራት ድርድር የሥራ ዘርፍ ዳይሬክተር የኾኑትን ሚስ ማይካ ኦሺካዋን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። ሁለቱ ባለስልጣናት ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅትን የምትቀላቀልበትን ሂደት ማፋጠን በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ሚኒስትር ዴኤታው በኢትዮጵያ በኩል እየተደረጉ ያሉ ቴክኒካል ድርድሮች በፍጥነት አልቀው የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል በመንግሥት በኩል ቁርጠኝነት እና ዝግጁነት እንዳለ ተናግረዋል። የዓለም ንግድ ድርጅትን መቀላቀል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ቁልፍ አጀንዳ እንደመኾኑም በዚህ ረገድ ከንግድ እና ፋይናንስ ዘርፉ ጋር የተያያዙ አስፈላጊ የፖሊሲ ማሻሻያዎች እና ውሳኔዎች መከናዎናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የትልቅ ኢኮኖሚ ባለቤት ሀገር እንደመኾኗ የዓለም ንግድ ድርጅትን መቀላቀሏ ለድርጅቱ መጠናከር ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ገልጸዋል። ዳይሬክተር ማይካ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ድርጅቱን ለመቀላቀል የጀመረችውን የድርድር ሂደት ለማፋጠን የድርጅታቸው ሴክሬታሪያት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መኾኑን ጠቅሰዋል። ድጋፉን አጠናክሮ ለማስቀጠልም ቃል ገብተዋል።
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ባገኘነው መረጃ መሠረትም ሁለቱ ባለሥልጣናት ሂደቱን ለማገዝ በሚያስችሉ ዝርዝር የቴክኒክ ሥራዎች ላይ ምክክር አድርገዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
