
ባሕር ዳር: ግንቦት 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በብልፅግና ፓርቲ እና በሕወሃት መካከል የተጀመረው የፓርቲ ለፓርቲ ፓለቲካዊ ውይይት ለሦስተኛ ጊዜ በመቐለ ከተማ በዛሬው ዕለት ግንቦት 7/2016 ተካሂዷል::በውይይቱም ቀደም ሲል የተደረሰውን የፓርቲ ለፓርቲ የግንኙነት መርሆዎች በማስታወስና የተጀመረውን ዋና ዋና አጀንዳዎች የመለየት ሂደት በማጠናቀቅ በአጀንዳዎቹ ቅደም ተከተል ላይ ከመከሩ በኃላ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል::
በመጀመርያ አጀንዳነት የተለየውን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ጋር ተያይዞ በዝርዝር ውይይት በማድረግ ሁለቱም ፓርቲዎች ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ በጋራ በቁርጠኝነት ለመሥራት በመስማማት፤ በመጨረሻም :-
1. በቅርቡ በራያ የተፈጠረውን የግጭት ክስተት በተመለከተ በዝርዝር ውይይት በማካሄድ፣ ክስተቱ መፈጠር ያልነበረበትና ከጀመርነው ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ ሂደት ጋር የሚቃረን እንደሆነ መግባባት ላይ ደርሰዋል::
2. ማናቸውንም ጉዳዮች በሰላማዊ መንገድና በውይይት እየፈቱ ለመሄድ ሁለቱም አካላት የበኩላቸውን ፓለቲካዊ ድርሻ ለመወጣትና በቁርጠኝነት ለመሥራት ተስማምተዋል:: በተያያዘም የሚኖሩ የኮሙኒኬሽን ሥራዎች የሰላም ሂደቱን የሚደግፉ እና ግጭት ቀስቃሽ ከሆኑ ንግግሮችና ይዘቶች የተቆጠቡ እንዲሆኑ መግባባት ላይ ደርሰዋል ::
3. ማናቸውንም ግጭት የሚፈጥሩ አዝማምያዎች በጋራ ለመከላከል እና ከተፈጠሩም በፍጥነት ለመቆጣጠር በቁርጠኝነት ለመሥራት ተስማምተዋል::
4. የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ወደ መሬት ለማውረድ እየተሠሩ ላሉ ሥራዎች ስኬት ምቹ ፓለቲካዊ ሁኔታ ለመፍጠር ሁለቱም ፓርቲዎች ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መስማማት ላይ ደርሰዋል::
በቀጣይም በሌሎች አጀንዳዎች ላይ ለመወያየት በመስማማት የእለቱን ውይይት አጠናቅቋል::
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
