“ያደገ መንግሥት ትልቁ እና የመጨረሻው ጉዳይ ዜጎችን በፍጥነት እና በታማኝነት አገልግሎት መስጠት ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ

35

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ የአዘርባጃን የሥራ ጉብኝታቸውን እና የተደረጉ የጋራ ስምምነቶችን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በማብራሪያቸውም በሀገሪቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥን መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡ የአገልግሎት አሰጣጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጉዳይን የሚጨርስ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ በአንድ ቦታ የሚሰጡ አገልግሎቶች፣ ሕዝብ ቅሬታ ለሚነሳባቸው እና ሰልፍ ለሚታይባቸው አካባቢዎች መፍትሔ እንደሚሰጥ ነው ያነሱት፡፡

የአዘርባጃን የሕዝብ አሥተዳደር በጣም ጥሩ መኾኑን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ አገልግሎት እርካታ 99 ነጥብ 8 በመቶ መድረሳቸው እንደተገለጸላቸውም አንስተዋል፡፡ በአዘርባጃን እየተሰጠ ያለውን ዘመናዊ አገልግሎት አሰጣጥ መመልከታቸውን እና በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውንም ገልጸዋል፡፡ ዘመናዊ የአገልገሎት አሰጣጥ ሥርዓቶችን በማለማመድ፣ የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ትልቅ ሥራ ለመሥራት ያነሳሳል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ የሲቭል ሰርቪስ ለውጦችን መጀመሯን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ልምዶችን በመውሰድ ለውጦችን ለማምጣት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ መንግሥት በብዙ ሥራዎች ላይ ለውጥ እንዳመጣ ሁሉ የሲቪል ሰርቪስ እና የዲጂታል ኢትዮጵያ ለውጦችን አቀናጅቶ በመጠቀም በጋራ ወደ ትልቅ ምዕራፍ ይሻገራል ነው ያሉት፡፡

ሥራው ቁርጠኝነት የሚጠይቅ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ መንግሥት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እና ዲጂታላይዝ ለማድረግ ወስኖ ወደ ሥራ መግባቱን አመላክተዋል፡፡ አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን የዜጎችን የመገልገል መብት ከመመለስ በተጨማሪ ያደገ ማኅበረሰብ፣ ያደገ ሀገር፣ ያደገ መንግሥት ትልቁ እና የመጨረሻው ጉዳይ ዜጎችን በፍጥነት እና በታማኝነት አገልግሎት መስጠት ነው ብለዋል፡፡ ስምንት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ላይ ሥራ መጀመራቸውንም አመላክተዋል፡፡ የተጀመረው ሥራ እያደገ እና እየሠፋ እንደሚሄድም ገልጸዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleባለፉት ዘጠኝ ወራት በትምህርት ዘርፉ የተሠሩ ሥራዎች ውጤታማ እንደነበሩ ትምህርት ቢሮ ገለጸ፡፡
Next articleበብልፅግና ፓርቲ እና በሕወሃት መካከል የተጀመረው የፓርቲ ለፓርቲ ፓለቲካዊ ውይይት ተካሄደ።