
ባሕር ዳር: ግንቦት 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከሰሜን ሸዋ፣ ከምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ከደብረብርሃን እና ደብረማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የትምህርት መሪዎች፣ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህራን እና ሱፐር ቫይዘሮች ጋር የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እያካሄደ ነው።
በዚህ የዘጠኝ ወራት የዕቅድ ግምገማ በኅብረተሰብ ተሳትፎ የትምህርት ቤቶችን ገጽታ የመቀየር፣ የመገንባት እና ለመማር ማስተማር ሥራው አጋዥ የኾኑ ግብዓትን የማሟላት ሥራዎች መሠራታቸው ተነግሯል። በተያዘው የትምህርት ዘመን የመምህራንን እና የትምህርት መሪዎችን በማሟላት እና አዲሱን የትምህርት ሥርዓት መሠረት በማድረግ የተሻለ ሥልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ አበረታች ሥራ መሠራቱ ተገልጿል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራቶች በትምህርቱ ዘርፍ በተለይም የትምህርት ቤቶችን ገጽታ በመቀየር፤ ምንም እንኳ ክልሉ በፀጥታ ችግር ውስጥ ቢኾንም የተማሪዎችን ውጤት በማሻሻል፤ ሙሉ ጊዜን ሳይሸራርፉ የመማር ማስተማር ሥራውን በመከወን እንዲሁም የትምህርት ቤቶችን ምገባ ከፍ በማድረግ ረገድ የተገኘው ውጤት አበረታች መኾኑ በሪፓርቱ ላይ ቀርቧል።
በትምህርት ዘመኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራቶች የመጸሐፍት አቅርቦት እና ጥምርታ ችግርን በመፍታት፣ የላብራቶሪ ግብዓቶችን በማሟላት፣ ለልዩ ፍላጎት ትምህርት ልዩ ትኩረት በመስጠት እና የጎልማሶችን ትምህርትም በማጠናከር የተሠራው ሥራ አበረታች መኾኑ ተነግሯል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራቶች በክልሉ የገጠመውን የፀጥታ ችግር በመቋቋም በተለይም ለሚሰጡ ክልላዊ እና ሀገራዊ ፈተናዎች የሚደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች በጥሩ ሂደት ላይ እንደሚገኙም ተመላክቷል፡፡
በቀሪዎቹ ጊዜያትም ያጋጠሙ ፈተናዎችን እና ችግሮችን በጽናት በማለፍ በዕውቀት፣ በአመለካከት እና በክህሎት የዳበረ ትውልድ የማፍራት ጥረቱ እንደሚቀጥልም ተገልጿል፡፡ ለዚህ ሥራ ስኬትም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረት ወሳኝ መኾኑ ተመላክቷል።
ዘጋቢ፡- ሰለሞን አሰፌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
