“ባለፈው ሳምንት በክልሉ ስኬታማ ሁነቶች ተካሂደዋል” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)

46

ባሕር ዳር: ግንቦት 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸውም በክልሉ ባለፉት ሳምንታት በርካታ ሁነቶች መካሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡ በጎንደር ከተማ የዲሞክራሲ ባሕል ግንባታ የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ መካሄዱን እና መሪዎች ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በተደረገው የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ውይይት ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ መሪዎች መገኘታቸውን አመላክተዋል፡፡

መሪዎቹ ከግምገማ ባለፈ በከተማዋ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን እና ታሪካዊ ስፍራዎችን መጎብኘታቸውንም ገልጸዋል፡፡ ሁነቱ ሲካሄድ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች እንግዳ ተቀባይነታቸውን ያሳዩበት፣ እንግዶቹም የጎንደር ከተማን እውነታ ያዩበት፣ እንደሚነዛው ሀሰተኛ መረጃ ሳይኾን ሰላማዊ መኾኗን፣ ከሕግ ማስከበር ጎን ለጎን የልማት ሥራዎች እየተሠሩባት ያለች ከተማ መኾኗን ያረጋገጡበት ነው ብለዋል፡፡

ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ እንግዶች በከተማዋ መልካም ነገር ይዘው መመለሳቸውን እና ከአማራ ክልል ጎን መኾናቸውን ያረጋገጡበት እንደነበርም አመላክተዋል፡፡ የጎንደር ከተማ ሕዝብ ላሳየው ወንድማማችነት፣ ፍቅር እና እንግዳ ተቀባይነት ምሥጋና ይገባዋል ነው ያሉት፡፡ ዶክተር መንገሻ ፈንታው የከተማዋ መሪዎች ላሳዩት ቁርጠኝነት እና ሰላም ማስከበር ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ የጸጥታ ኃይሎችም የጸጥታ ሁኔታውን አስተማማኝ በማድረግ ከተማዋ ወደ ልማት እንድትገባ ላደረጉት አስተዋጽኦ ምሥጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡

በሳምንቱ በጎርጎራ የተካሄደው ሁነት ሌላኛው ትኩረት የሳበ ጉዳይ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ የጎርጎራ ፕሮጀክት በርካታ ነገሮችን አቀናጅቶ የያዘ፣ የቱሪዝም ማዕከል የኾነ፣ የቀደምት ታሪኩን ክብር በጠበቀ መልኩ የተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ.ር) ጨምሮ የሀገሪቱ ከፍተኛ መሪዎች መጎብኘታቸውን እና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም የገመገሙበት መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡

የጣናን ልዩ መስህብ የያዘ ከፍተኛ ሥራ የተሠራበት ነው ብለዋል፡፡ ጎርጎራ የቱሪስት መስህብ የኾነ፣ ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታ ያለው፣ አካባቢውን የሚያሳምር፣ ለአካባቢው ማኅበረሰብም ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ የሚያራዝም መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ በታላቁ ወንዝ ላይ የተገነባውን የታላቁ ድልድይ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ሌላኛው በክልሉ የተካሄደው ትልቁ ሁነት መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ድልድዩ ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታው ለባሕር ዳር ከተማ ብቻ ሳይኾን ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ነው ብለዋል፡፡ ክልሉ ከኤርትራ እና ከሱዳን ጋር እንደሚዋሰን የተናገሩት ኀላፊው የንግድ ሥርዓቱን የሚያሳልጥ፣ ለቱሪዝም እንቅስቃሴ ትልቅ አቅም ያለው መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ድልድዩ ያማረ ውበት ያለው፣ ቀልብ የሚስብ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

ያለ ምንም ጥገና ከመቶ ዓመታት በላይ አገልግሎት የሚሰጥ ለትውልድ የሚሻገር ድልድይ ነው ብለዋል፡፡ መንግሥት ትልልቅ ፖሮጀክቶችን በፍጥነት እና በጥራት እንደሚያጠናቅቅ ማሳያ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ታላቁ ድልድይ ሲመረቅ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች እንግዶችን በፍቅር መቀበላቸውንም አስታውቀዋል፡፡ የምርቃ ሥነ ሥርዓቱ በሰላም ተጀምሮ በሰላም መጠናቀቁንም አስታውሰዋል፡፡

ከምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ጋር ተያይዞ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚናፈሱ ሃሰተኛ መረጃዎች አሉ ያሉት ኀላፊው የሚናፈሱ ሃሰተኛ መረጃዎች መሬት ላይ የሌሉ እና ሕዝብ የሚታዘባቸው መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ያለ ምንም እንከን ተካሂዷል፤ በሰላም ተጀምሮ ያለ ምንም ችግር በሰላም ተጠናቅቋል፤ የተነዛው ሃሰተኛ ወሬ ግን አሳፋሪ ነው ብለዋል፡፡ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ለተገኙ እንግዶችም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

በየትኛውም አካባቢ የሚሰራጩ ሃሰተኛ መረጃዎችን ማመን እንደማይገባም አሳስበዋል፡፡ በድልድዩ ምርቃት ዙሩያ የተነዛው ሀሰተኛ መረጃ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጬ ሌሎች መረጃዎችም ሀሰተኛ መኾናቸውን ትምህርት የሚሰጥ፣ ያን ያወሩ እና ያስወሩ አካላት ዳግም ወደ ሚዲያ ቀርበው ሀሰተኛ መረጃን ለመስጠት ሞራል እንዳይኖራቸው የሚያደርግ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝቶ ፍቅሩን እና አክብሮቱን ለገለጸው የባሕር ዳር ከተማ ሕዝብም ምሥጋና ይገበዋል ነው ያሉት፡፡

ክልሉ ሰላም ነው፣ የልማት ሥራዎቻችን እየሠራን ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም ሌሎች ፕሮጀክቶች እንደሚመረቁ ነው የተናገሩት፡፡ የታየው እንግዳ ተቀባይነት እና ፍቅር በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡ ከድልድዩ ምርቃት ጎን ለጎን የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መሪነት የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አሥፈጻሚ አባላት ያስጀመሩት ንቅናቄ በክልሉ የተካሄደ ሌላኛው ሁነት ነበር ተብሏል፡፡ በዘመቻው የክልሉ መሪዎች እና ሕዝብ መሳተፉንም አስታውቀዋል፡፡ በንቅናቄው ስኬታማ ውጤት መመዝገቡን እና ስንተባበር የማንሻገረው ነገር አለመኖሩን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ በሰሜን ሸዋ ዞን ቡልጋ የተለያዩ ፕሮጀክቶች መመረቃቸውን እና መመልከታቸውን አንስተዋል፡፡ በሰሜን ሸዋ ዞን በተለይም በደብረ ብርሃን በርካታ ፋብሪካዎች መኖራቸውን አመላክተዋል፡፡ ፋብሪካዎቹ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት የውጭ ምንዛሬን የሚያስቀሩ፣ ለውጭ ገበያ በማቅረብም የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ናቸው ብለዋል፡፡ የግብርና ግብዓቶችን በመጠቀም አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል፡፡

የሥራ እድል ፈጠራ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ነው የተናገሩት፡፡ የፕሮጀክቶቹ ምረቃት የክልሉን ሰላም ያሳዩ፣ ኢንቨስተሮች እንዲመጡ መደላድል የሚፈጥር፣ የሰሜን ሸዋ ሕዝብ እንግዳ ተቀባይ እና ሰላማዊ መኾኑን ያሳዩ ናቸው ብለዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት የሰሜን ሸዋ ሕዝብ ላሳየው መልካም ነገር ሁሉ ምሥጋና ያቀርባል ነው ያሉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከአማራ ክልል ከተመለሱ በኋላ በጎንደር ከተማ የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን ገምግመው አቅጣጫ ማስቀመጣቸውንም አንስተዋል፡፡ ላስቀመጡት አቅጣጫ ምሥጋና እናቀርባለን ነው ያሉት፡፡ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቁ እምነታችን ነው ብለዋል፡፡ በክልሉ የተከናወኑ ሁነቶች አመርቂ፣ የክልሉን ቁመና እና አሁናዊ እውነታ የሚያሳዩ መኾናቸውን አመላክተዋል፡፡

የክልሉ ሕዝብ እንቅፋት የሚኾኑ ኃይሎችን ማስቆም ይገባዋል ያሉት ኀላፊው ፕሪጀክቶች በቆሙ ቁጥር የክልሉ ሕዝብ ወደኃላ እየሄደ፣ ለተወሳሰቡ ችግሮች እየተጋለጠ ስለኾነ ሁሉም ትግል ሊያደርግ ይገባል ነው ያሉት፡፡ እንግዳ ተቀባዩ ሕዝብ ላደረገው ሁሉ እናመሠግናለን፣ በቀጣይም በለመደው እንግዳ ተቀባይነቱ፣ ሰላማዊነቱ እንዲቀጥል አደራ እላለሁ ብለዋል፡፡

በክልሉ ያለው የሕግ ማስከበር ሥራ ከበፊቱ እየተሻሻለ እና እያደገ መጥቷል ያሉት ዶክተር መንገሻ የልማት ሥራዎች እና የፕሮጀክት አፈጻጸሞች እየሰፋ መምጣቱን አስታውቀዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሥራ ከባቢን ምቹ ማድረግ ከቀዳሚ የትኩረት መስኮቻችን አንዱ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleባለፉት ዘጠኝ ወራት በትምህርት ዘርፉ የተሠሩ ሥራዎች ውጤታማ እንደነበሩ ትምህርት ቢሮ ገለጸ፡፡