
ባሕር ዳር: ግንቦት 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በያዝነው ዓመት በመስኖ ስንዴ ልማት እስካሁን 80 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሠብሠቡን ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ሚኒስቴርን የበጀት ዓመቱን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2 ነጥብ 97 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ገልጸው እስካሁን 80 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተሠብሥቧል ብለዋል። ባለፈው ዓመት 47 ሚሊዮን ኩንታል ከመስኖ ስንዴ መሠብሠቡን ገልጸው የዘንድሮው ምርት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ስለመጨመሩ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በሆልቲካልቸር ዘርፍ እንዲሁም የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርት በመጨመር ገበያን ለማረጋጋት የተሠራው ሥራ ውጤት ማስመዝገቡንም ጠቁመዋል። ከቡና እና ሻይ አንፃርም ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር የተሠራው ሥራ አበረታች ውጤት ማስመዝገቡን ጠቁመዋል። ወደ ውጭ ገበያ የተላከው ቡና ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 10 በመቶ ጭማሪ አንዳለው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ባለፈው የመኸር ምርት 17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሶ 506 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሠብሠብ መቻሉን ተናግረዋል። በግብርና የሚመዘገበው ዕድገት አጠቃላይ ለሀገሪቱ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው በማሰብ ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው ባለፉት አራት ዓመታት ግብርና በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን ሚኒስትሩ ገልጸው በዚህ ዓመት 6 በመቶ ዕድገት ያስመዘግባል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
