የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

82

ባሕር ዳር: ግንቦት 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ የተላለፉት ውሳኔዎች የሚከተሉት ናቸው፦

1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በአራት የፋይናንስ ድጋፍ እና ብድር ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ ለምስራቅ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ግሪድ ማጠናከሪያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ከአፍሪካ የልማት ባንክ የተገኘ የ52 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር፣ ለሥራ ፈጠራ እና የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል ከጣልያን መንግስት የተገኘ 10 ሚሊዮን ዩሮ፣ ለቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር የተገኘ 255 ሚሊዮን ዶላር አንዲሁም ለፓወር ሴክተር ሪፎርም፣ ኢንቨስትመንት እና ሞደርናይዜሽን ፕሮጀክት ምዕራፍ አንድ ማስፈፀሚያ የሚውል 393 ሚሊዮን ዶላር ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር የተደረጉ የብድር ናቸው፡፡ ከአፍሪካ የልማት ባንክ የተገኘው ብድር 0.01% ወለድ እና ብድሩን በማስተዳደር ረገድ ለሚወጡ ወጭዎች 0.1% የአገልግሎት ክፍያ የሚታሰብበት ኾኖ የ15 ዓመታት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ40 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው፡፡ ከጣልያን መንግስት የተገኘው ብድር ከወለድ ነጻ ከመኾኑም በላይ የ16 ዓመት የችሮታ ጊዜ ያለው እና በ30 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው፡፡ ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር የተገኙት ብድሮች ወለድ የማይታሰብባቸው፣ ብድሮቹን በማስተዳደር ረገድ ለሚወጡ ወጪዎች 0.75% የአገልግሎት ክፍያ ብቻ የሚታሰብባቸው፣ የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜ ያላቸው እና በ38 ዓመት ተከፍለው የሚጠናቀቁ ናቸው፡፡ ምክር ቤቱ ሁሉም ብድሮች ከሀገራችን የብድር አስተዳደር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ መኾናቸውን በማረጋገጥ በሙሉ ድምጽ ተቀብሎ ረቂቅ አዋጆቹ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

2. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ባቀረባቸው ሦስት ረቂቅ አዋጆች እና አንድ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡

የመጀመሪያው የኢሚግሬሽን አዋጅ ቁጥር 354/1995ን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ሲኾን መሠረታዊ ከኾኑ መብቶች አንዱ የኾነውን የመዘዋወር ነፃነትን ለማስከበር፣ የኢሜግሬሽን አገልግሎቶችን ለኢትዮጵያዊን እና ለውጭ ሀገር ዜጎች በተሻለ ጥራት እና ቅልጥፍና መስጠት እንዲቻል፣ የተቀናጀ የድንበር ቁጥጥር እና አስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋት የተሟላ የመንገደኛ ቅድመ ጉዞ መረጃ መያዝ አስፈላጊ በመኾኑ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡

ሁለተኛው የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎትን በድጋሚ ለማቋቋም የወጣ ረቂቅ አዋጅ ሲኾን ተቋሙ በሚሰጠው አገልግሎት የዜጎችን ፍላጎት የሚያሟላ፣ የግልጽነት እና የተጠያቂነት ሥርዓት የሰፈነበት እንዲኾን፣ የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም እና ደኅንነት በሚገባ የሚያስጠብቅ ስልጣን እና አደረጃጀት እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ በመኾኑ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡

3. ሦስተኛው የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ ረቂቅ አዋጅ ሲኾን የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ ሥርዓትን በማሻሻል አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ፣ ተደራሽ፣ ግልጽ እና ውጤታማ ማድረግ፣ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መሠረታዊ የዜጎችን መብት እና ነፃነት ለማክበር እና ለማስከበር ሁሉን አቀፍ የምዝገባ ስርዓት መዘርጋት የሚገባ በመኾኑ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በቀረቡት ሦስት ረቂቅ አዋጆች ላይ በሰፊው ከተወያያ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

4. አራተኛው ምክር ቤቱ የተወያየበት ጉዳይ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚያስከፍለውን ክፍያ ለመወሰን በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ ተቋሙ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ማስፋት፣ የአገልግሎቶቹን የጥራት ደረጃ ማሻሻል፣ ብሎም የተጠቃሚውን ማኅበረሰብ አቅም ባገናዘበ መልኩ አገልግሎት ለመስጠት ያወጡትን ወጪ መሸፈን የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

5. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያያው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቀረቡ ሁለት የሁለትዮሽ ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እና የሩሲያ መንግሥታት መካከል ያለውን የአየር አገልግሎት ስምምነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተፈረመ ስምምነት ነው፡፡ ሌላው ስምምነት በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዥያ መንግሥታት መካከል የዲፕሎማቲክ እና ሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛን ለማስቀረት የተደረገ ስምምነት ነው፡፡ ምክር ቤቱም ስምምነቶቹ ቢጸድቁ ኢትዮጵያ ከሁለቱ ሀገራት ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ እና በሀገራቱ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ትስስር የሚያጎለብቱ መኾኑን በመገንዘብ፣ የስምምነቶቹ መጽደቅ የሀገራችንን ጥቅም የማይጎዳ እና የተለየ ግዴታም የማያስከትል መኾኑን በማረጋገጥ ረቂቅ አዋጆቹን በሙሉ ድምጽ አጽድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleተቋማትን በሥራዎቻቸው የመለካት ልምድ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተጠቆመ።
Next article“80 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ተሠብሥቧል” ግብርና ሚኒስቴር