ተቋማትን በሥራዎቻቸው የመለካት ልምድ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተጠቆመ።

31

ባሕር ዳር: ግንቦት 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል የግብርና ተጠሪ ተቋማት መሪዎች የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸማቸውን ገምግመዋል። በግምገማዊ ውይይቱ ተቋማትን በሥራዎቻቸው የመለካት ልምድ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) አሳስበዋል።

በግምገማዊ ውይይቱ የገጠር ዘርፍ ተቋማት ኀላፊዎች እና ዳይሬክተሮች ተሳትፈዋል። ተቋማቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የሠሯቸውን ዋና ዋና ሥራዎች እና የታዩ ውጤቶችም ተነስተዋል። አሠራርን በማዘመን፣ በየተዋረዱ ያሉትን ተቋማት በመደገፍ፣ የክልል አቅም፣ ችግር እና ክፍተትን ተረድቶ አቅምን ወደ ዕድል በመቀየር፣ ኅብረተሰብን በማሳተፍ፣ ክልሉ ካጋጠመው የጸጥታ መደፍረስ አኳያ አቅምን አሟጦ አገልግሎት መስጠት፣ ሰላም እንዲሰፍን መሥራት፣ ዐበይት ተግባራትን ለይቶ ከዓላማ ጋር አስተሳስሮ በመሥራት በኩልም የተሠሩ ሥራዎች ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

ውይይቱን የመሩት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የግብርና ዘርፉ የክልሉ ከፍተኛ በጀት የሚፈስስበት እና አብዛኛው ማኅበረሰብ የሚገለገልበት ዘርፍ መኾኑን ጠቅሰው አብዛኛው ሥራ የሚሠራው እስከ ቀበሌ ድረስ ወርዶ በመደገፍ ነው ብለዋል። ጠንካራ የድጋፍ እና ክትትል ሥርዓት አለመኖር ዘርፉን ይጎዳዋልም ብለዋል።

ተቋማትን በሥራቸው የመለካት ልምድ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያሳሰቡት ዶክተር ድረስ ክልሉ ያለበትን ችግር በመረዳት ወደፊት ለማስፈንጠር ማሰብ እና መሥራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። የአፈጻጸም ውስንነት እንዳይኖር ሴክተሮች እኩል ታች ድረስ ወርደው መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ነው ኀላፊው ያሳሰቡት።

ዶክተር ድረስ በቀጣይም፦
👉 መሪው በየ15 ቀኑ ሥራን እየገመገመ መምራት እንዲችል፤
👉 የተቋማትን አሠራር በቴክኖሎጂ በማዘመን እንዲሠራ፤
👉 የተጠናከረ ድጋፍ በማድረግ የዞኖችን አቅም እና ውጤታማነት ማሳደግ እንዲቻል፤
👉 የክልሉን አቅም ታሳቢ ያደረገ ሥራ እንዲሠራ፤
👉 በልማት ሥራዎች ላይ የኅብረተሰብ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤
👉 ልማት የሚፋጠንበትን አማራጮች አልሞ እና አቅዶ መሥራት እንዲቻል አቅጣጫ ሰጥተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዶክተር አሕመዲን መሐመድ የተመራ የአማራ ክልል የልዑካን ቡድን በኬንያ የልምድ ልውውጥ እያካሄደ ነው።
Next articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።