
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) የተመራ ልዑክ ነው ኬንያ በመገኝት በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የልምድ ልውውጥ እያካሄደ የሚገኘው።
የልዑካን ቡድኑ በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ “ኢስትሪፕ” በሚል ፕሮጀከት ማዕቀፍ የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት እና ሥልጠና ተደራሽነትን፣ ጥራትን አና ቀጣናዊ ትስስርን ለማሳደግ በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ ሀገራት መካከል ማለትም በኢትዮጵያ፣ ኬንያ አና ታንዛንያ በተመረጡ 16 ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጆች ውስጥ እየተተገበረ ነው።
በዚህ ፕሮጀክት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተመረጡ ሰባት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅች ውስጥ የኮምቦልቻ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በአውቶሞቲቭ ዘርፍ የምሥራቅ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል ኾኖ በውድድር አሽንፎ በመመረጡ በፕሮግራሙ 900 ሚሊዮን ብር ተመድቦለት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።
በአማራ ክልል በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) የተመራው የልዑካን ቡድን የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ በላይ ዘለቀ፣ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሐመድአሚን የሱፍ እና የኮምቦልቻ ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጅ አመራሮችን ያካተተ ነው።
የጉብኝቱ ዓላማ በኬንያ ከሚገኙ እና በዚህ ፕሮጀከት ታቅፈው የተሻለ አፈፃፀም ካላቸው ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ልምድ ለመቅሰም ያለመ መኾኑ ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
