በማሽላ ዘር ብዜት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።

19

ከሚሴ: ግንቦት 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደርም ኾነ እንደ ክልል ያለውን የዘር አቅርቦት አጥረት ለመቅረፍ ሥራዎች መሠራታቸው ተገልጿል። በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ የተመራ ልዑክ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የተመረተውን የማሽላ ምርጥ ዘር ብዜት ጎብኝቷል።

የደዋጨፋ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እንድሪስ መሐመድ እንደ ዞን ያለውን የማሽላ ምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር በመገንዘብ ወረዳቸው ከአርሶ አደሮች ጋር መግባባት በመፍጠር በ2014/15 የምርት ዘመን 103 ሄክታር መሬት በምርጥ ዘር ብዜት ተሸፍኗል። አርሶ አደሩ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንዲያገኝ መደረጉንም ገልጸዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ ሀሰን ሰይድ ወደ ዘር ብዜት ሥራ የተገባበት ዋነኛ ምክንያት በአካባቢው ያለውን የዘር አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ታስቦ መኾኑን ተናግረዋል። በ2015/16 የምርት ዘመን ከ1 ሺህ 600 ኩንታል በላይ ዘር በማባዛት አርሶ አደሩ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲያገኝ መደረጉን ኀላፊው ገልጸዋል።

በዘር ብዜቱ ከአካባቢው አልፎ እንደ ክልል ያለውን የማሽላ ምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር መቅረፍ እንደተቻለም ተናግረዋል። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሰብል ልማት ባለሙያ ብርሀኑ ሞገስ የዘር ብዜቱ ሲከናወን ከቀበሌ እስከ ዞን ያለው ባለሙያ ተገቢውን ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ዘሩን ከመጤ አረም መጠበቅን ጨምሮ ማሟላት ያለበትን ሁሉ አሟልቶ ፈቃድ ያገኘ መኾኑንም አስገንዝበዋል።

በዘንድሮው ዓመት ከ600 በላይ ሄክታር በማሽላ ዘር ብዜት በመሸፈን ከ20 ሺህ በላይ ኩንታል ምርት በመሠብሠብ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱ ተገልጿል።

ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሂም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የመቶ ዓመታት መሻገሪያ፤ የአዲስ ውበት መደረቢያ”
Next articleበዶክተር አሕመዲን መሐመድ የተመራ የአማራ ክልል የልዑካን ቡድን በኬንያ የልምድ ልውውጥ እያካሄደ ነው።