“የመቶ ዓመታት መሻገሪያ፤ የአዲስ ውበት መደረቢያ”

80

ባሕር ዳር: ግንቦት 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለተዋበችው ከተማ ተጨማሪ ውበት ተሰጣት፣ ከጌጥ ላይ ጌጥ ተጨመራት፣ ከመወደድ ላይ ሌላ መወደድ ታከላት፡፡  ጠባቂዎች በዙሪያ ገባው እንደሚጠብቋት፣ የወርቅ ምንጣፍ እንደተነጠፈላት፣ በሰርክ ያማሩ ሽቱዎች እንደሚረጩባት፣ ንጉሥና ንግሥት እንደሚቀመጡባት የተዋበች እልፍኝ አስመስሎ አስዋባት፡፡

ያዩዋት ሁሉ ውቢት እያሉ ያደንቋታል፤ ባሕር ሰንጥቀው፣ የብስ አቋርጠው፣ በሰማይም በርረው እየመጡ ሊከትሙባት፣ የውበቷን ማማር እያዩ ሊደመሙባት፣ በእቅፏ ሥር ተወሽቀው ሊሰነብቱባት፣ በውበቷ እና በፍቅሯ ሀሴትን ሊያገኙባት ይመኟታል፡፡ ይወዷታል፡፡ እድል ገጥሟቸው፣ ጊዜ ፈቅዶላቸው በመጡ ጊዜ በደስታ እና በፍቅር ይከርሙባታል፤ የማይጠፋ ትዝታ ሸምተውባት፤ በውበቷ ተውበውባት፣ በፍቅሯ ደስ ተሰኝተውባት፤ ዳግም ያገናኘን ብለዋት ይለዩዋታል፡፡

ረጅሙን ወንዝ ታጥቃ ትኖራች፣ በምስጢራዊ ሐይቅ ትታጀባለች፣ ከዓመት ዓመት ውበትን በሚሰጡ ዘንባባዎቿ ትዋባለች፣ ባማሩ ጎዳናዎቿ ትደምቃለች፣ ታሪክ በሚነገርባቸው ተራራዎቿ ግርማን ትለብሳለች፡፡  ጣና እያሳመራት፣ ግዮን ውበትን፣ ዓይነ ግቡነትን እያስታጠቃት ለዓመታት ኖራለች፡፡ የጣና ዳር እመቤት፣ የግዮን ንግሥት እያሉ ያሞግሷታል ባሕርዳርን፡፡ 

“ላለው ይጨመርለታል” እንዳለ መጽሐፍ ካላት ውበት፣ ከሚያሳሳ መወደዷ በላይ ሌላ ውበት ተጨምሮላታል። በጣና የተሰጠችውን ውበት፣ በግዮን የተቸረችውን ዓይነ ግቡነት ያዩ ሁሉ አድንቀው ሳይጨርሱት ሌላው ውበት ተደረበላት። የተሰጠችው አዲስ ውበት መወደድን የሚሰጣት፣ እዩኝ እዩኝ የሚያስብላት ብቻ አይደለም።  ለመቶ ዓመታት የምትሸጋገርበት፣ የተራራቀውን የምታገናኝበት፣ በአሻገር ያለውን በናፍቆት የምትጠራበት፣ የዳር ሀገሩን ወደመሀል ሀገር፣ የመሀል ሀገሩን ወደ ዳር ሀገር የምትወስድበት፣ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር በመንገድ የምትተሳሰርበት፣ ያላትን ለሌሎች አፍሪካውያን ሀገራት የምታሻግርበት፣ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም የምትቀበልበት ነው እንጂ።

በዓለማችን በእርዝመቱ ወደር በማይገኝለት፣ ከተመረጡ አራት አፍላጋት መካከል  በግዮን ላይ የተሠራው ታላቁ ድልድይ በአንደኛው ማዶ ያለውን ወደ ሌላኛው ማዶ ከማሸጋገር፣ የተነፋፈቁትን ከማገናኘት  ያለፈ ነው ይሉታል። ለምን ቢሉ ውበትም ሃብትም፣ ተስፋም በረከትም ነውና።  የግዮን ወንዝ በመካከላቸው የሚያልፈው የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች  በአንድ ድልድይ እየተሻገሩ ዓመታትን አሳልፈዋል።  ይህ ድልድይ ለዓመታት ደጋፊ ምርኩዝ ያልተበጀለት፣ የሚያርፍበት ሌላ አጋዥ ያልተሠራለት ነበርና ነዋሪዎች ከዛሬ ነገ ይፈርሰ ይኾን እያሉ ለዓመታት ተጨንቀዋል። ዓመታት ተቆጥረው ዓመታት በተተኩ ቁጥር እድሜው እየረዘመ፣ ጫናው እየበዛበት በመሄዱ ነዋሪዎች እባካችሁን እዩልን፣ ለክፉ ቀን የሚኾን ተጨማሪ ድልድይ ሥሩልን ሲሉ ኖረዋል።

በከተማዋ በዓባይ  ላይ የነበረው አንድያ ድልድይ እክል በገጠመው ጊዜ ከወንዙ ዳር እና ዳር ቆመው የሚጨነቁት ብዙዎች ናቸው። ከወንዝ ማዶ ለማዶ ኾነው  እየተያዩ የዋሉት፣ ሳይገናኙም ያደሩት ብዙዎች ነበሩ።  አሁን ይህ ታሪክ ኾኗል። መጨነቁም ቀርቷል። እንዴት ካሉ በኢትዮጵያ ከተሠሩት ድልድዮች ሁሉ ያማረው እና የተዋበው ድልድይ ተሠርቷልና።

ከዓመታት በኋላ  የነዋሪዎች ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ በታላቁ ወንዝ ላይ ዘመኑን የዋጀ፣ ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ የተሠራ ታላቅ ድልድይ ተገንብቷል። ለዓመታት ሲጨነቁ የኖሩ ነዋሪዎችም እፎይ ብለዋል። ደስም ተሰኝተዋል።

ሼህ ሲራጅ አሕመዲን  ስለ ድልድዩ ግንባታ ምርቃት ሲናገሩ ይህ ታላቅ ደስታ ነው። ለዓመታት የነበረ ጥያቄ ነው። ጥያቄው ምላሽ በማግኘቱ ደስ ብሎኛል። ይህ የተሠራው ድልድይ ለልጅ ልጅ የሚኾን ነው ይላሉ። ከአሁን ቀደም የነበረውን ሲያስታውሱ ከጎንደር ኖረን  ስንመለስ በዚያ ጠባብ ድልድይ ተሰልፈን እንቆማለን። ትራፊኮች ሲያስተናብሩ እስከ ምሽት አንድ ሰዓት እናመሻለን። አሁን ግን በሰከንድ እና በደቂቃ ከምናልፍበት ጊዜ ደርሰናል ነው ያሉት።

የቀደመው መጨናነቅ፣ ከዛሬ ነገ ይሰበር ይኾን የሚል ሀሳብ ፈተና እንደነበርም አስታውሰዋል። ሀገር ሰላም ቢኾን ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች ሥራዎችንም የማየት ተስፋ እንዳላቸውም ተናግረዋል።

ወይዘሮ ትዕግሥት ዓለሙ  ደግሞ ይሄን በማየታችን ደስ ብሎናል ነው ያሉት። ሰላም ሲኖር ነው ሁሉም ነገር የሚኖረው፣ አንድነት እና ፍቅር ያሸንፋል። ሰላም ሲኖር ሁሉም ይኖራል። ሰላም ሲኖር የተጀመሩት ይፈጸማሉ  ይላሉ። ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ደሳለኝ ድረስ ውብ የኾነውን  እና ትልቁን ድልድይ በማየታችን ትልቅ ደስታ ተሰምቶናል። ይህ የዓመታት ጥያቄ ነበር። ጥያቄው ተፈትቶ በማየታችን ደስተኞች ነን ነው ያሉት።

የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በታላቁ ወንዝ ላይ የተገነባው ታላቁ ድልድይ ዝም ብሎ ድልድይ ብቻ  ሳይኾን ከድልድይ ባሻገር እንደኾነ ነው የተናገሩት። ድልድዩ በፈተና አልፎ ለምርቃት የበቃ፣  በኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ታሪክ ልዩ ቦታ ባለው የዓባይ ወንዝ ላይ መገንባቱ ለየት የሚያደርገው መኾኑንም ገልጸዋል። ማድረግ እንችላለን የሚለውን ደጋግመን ያሳየንበት ነውም ይሉታል።

ለከተማዋ ከውበት በላይ ውበት ያጎናጽፋታል፣  ልዩ ድምቀት እና ስጦታ ነው። ድልድዩ ለከተማዋ እንደ አንድ የቱሪስት መዳረሻ ኾኖ እንደሚያገለግልም ተስፋችን ነው ብለውታል። ከጣና እና ከዓባይ፣ ከዘንባባዎቿ፣ ከአሳዎቿ፣ ከአማሩት ውብ ሥፍራዎቿ በተጨማሪ ሌላ ውበት ተሰጥታለች እና ጎብኚዎች ወደ ድልድዩ እንደሚጎርፉ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሙሐመድ አብዱራህማን  ስለ ድልድዩ ሲገልጹ   380 ሜትር ርዝመት፣ 43 ሜትር ስፋት አለው። በግራና በቀኝ በአንድ ጊዜ ስድስት ተሽከርካሪዎችን ማስተላለፍ ይችላል።  ታሪካዊውን  የቤዛዊት ቤተመንግሥትን  ያስተሳስራል፣ ድልድዩ መሠረታዊ ጥገና ሳይጠይቅ ከመቶ ዓመታት በላይ እንዲያገለግል ተደርጎ፣ ጥራቱን ጠብቆ የተገነባ ነው ይላሉ።  መሠረታዊ ጥገና ሲደረግለት ደግሞ የአገልግሎት እድሜው ከተባለው በላይ ይጨምራል።

ኢንጂነሩ እንደሚሉት ለግንባታው ከ54 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ አርማታ፣ ከ90 ሺህ ቶን በላይ ብረት፣ ከ500 ቶን በላይ መወጠሪያ ገመዶችን እንደዋና ግብዓት ተጠቅሟል።  ዲያሜትራቸው 1 ነጥብ 8 ሜትር የኾኑ፣ ከመሬት በታች 24 ሜትር ጥልቀት  ድረስ የተቀበሩ 88 መሠረቶች ላይ  ደግሞ ቆሟል።

የድልድዩ የላይኛው ክፍል በ72 ኬብሎች የተወጠረ ነው።  ጠቅላላ ክብደቱ በኬብሎቹ አማካኝነት ወደ ቋሚ መሰሶዎች እንዲተላለፍ ተደርጎ ከምሰሶው ወደ መሠረት እንዲዘልቅ ተደርጎ ተሠርቷል።  አዲስ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተሠራ  ነው፣ የትራፊክ ፍሰቱን ከማሳለጥ ባሻገር የተለያየ መስተጋብር መስጠት የሚችሉ መብራቶች የተገጠሙለትም ነው፣ የተለያዩ ቀለም ያላቸው መብራቶች በተለይም በምሽት ሲበሩ ልዩ ያደርጉታል፣ ለከተማዋም ልዩ ውበት ይሰጣታል።  ይሄም በመኾኑ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ከተሠሩ ድልድዮች ሁሉ  የተለየ ያደርገዋል  ይላሉ።
ድልድዩ ተጀምሮ እኪመረቅ ድረስ ባለሥልጣናት፣ ምሁራን እና ነዋሪዎች ጎብኝተውታል።  አይቶ ውበቱን ከማድነቅ ባለፈ ትምህርታዊ ጉብኝቶች ተደርገውበታል።  ይህም በመኾኑ  ጎብኚዎቹ ዕውቀትን ቀስመውበታል፣ ለቀጣይ ትውልድ መማሪያ፣  ራስን መቻያ፣ የቴክኖሎጂ መሸጋገርያ ይኾናል ነው የሚሉት።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ  ድልድዩን ሲገልጹት በዓይነቱም ኾነ በጥራቱ፣ በመጠኑም፣ በውበቱም ልዩ የኾነ፤  የረዥም ጊዜ የሕዝብ ጥያቄ የነበረ፣ የዚህ ዘመን ትውልድ አሻራ ያረፈበት፣  የመጪው ዘመን ትውልድ ውርስ እና ቅርስ የኾነ፣ ውብ በኾነ ሁኔታ የተገነባ የታላቅ ወንዝ ታላቅ ድልድይ ነው ይሉታል።

የዓባይ ድልድይ  አብዛኛውን የሀገሪቱን ክፍል ከሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ጋር የሚያስተሳስር በተለይም ደግሞ ለአማራ ክልል ልዩ ፀጋና በረከት ነው ብለን እናምናለን ነው የሚሉት።   ግዙፉና ውቡ ድልድይ ለክልሉ  ርእሰ መዲና ባሕር ዳር ቀደምት ምልክቷ ከኾኑት ከጣና ሐይቅ እና ዘንባባ ተክሏ ጋር ተሰላስሎ ዳግም ውብ እና ልዩ መለያ ምልክቷ ኾኖ በግርማ ሞገስ ቆሟል ነው ያሉት። ድንቁ ድልድይ በአንድ በኩል ራሱ የተጠራቀመ ሃብት፤ የጠራ እና ተራማጅ የኾነ ሃሳብ ውጤት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ራሱ ድልድዩ የቀጣዩን ጊዜ ልማት አሳላጭ እና የልማት የስበት ማዕከል ነው፡፡ በዚህም መደበኛ እና ከትራንስፖርት ጋር የተሳሰረው ፋይዳው እንደተጠበቀ ኾኖ በድልድዩ በአራቱም ማዕዘናት በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙት አካባቢዎች የመልማት ዕድላቸው ከፍተኛ ኾኗልም ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።

ድልድዩን ተንተርሶ ውብ እና ሥነ ምሕዳሩን በጠበቀ ሁኔታ የዓባይ ወንዝ ዳርቻ ልማትን ማከናወን ግድ በሚለን ሁኔታ ላይ እንድንገኝ ዕድል ፈጥሮልናል፣ ይህን ዕድል ሳናባክን ሥራ ላይ በማዋል የሕዝባችንን ተጠቃሚነት እና የከተማችንን ውበት በሚያስጠብቅ መልኩ አሁኑኑ ወደ ተግባር መግባት ይኖርብናል ነበር ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)  ድልድዩ ወገን ከወገን፣ ቤተሰብን ከቤተሰብ፣ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያገናኝ ንግድ የሚያሳልጥ በሰዎች አዕምሮ የታሰበ፣ ገንዘብ፣ ጉልበት ዕውቀት የፈሰሰበት ነው ብለውታል። እኛ ሁለት ድልድይ መገንባት እንፈልጋለን፣ ድልድይ እንገነባለን፣ መዝጊያ መከልከያ የኾነውን ግድግዳ እናፈርሳለን፣ የሕዝቦችን አንድነት እናረጋግጣለን የምንለው በድንጋይ እና በሲሚንቶ በሚሠራ ድልድይ ብቻ ሳይኾን በትርክት በሚገነባ ድልድይም ጭምር ነው ይላሉ።

በሕዝቦች መካከል በነበሩ አልባሌ ትርክቶች ምክንያት እየላላ ያለውን ትስስር ሊያጠናክር የሚችል የትርክት ድልድይ መገንባት እንፈልጋለን፣  ውቡና ትልቁ ድልድይ እኛነታችንን፣ ፍላጎታችንን፣ መሻታችንን ያሳያል፣ በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ ብልጽግናን እንመኛለን ስንል በንግግር ያልተገነዘቡን ሰዎች  በዚህ ድልድይ ብልጽግና ማለት ምን ማለት እንደኾነ እንዲረዱ  እፈልጋለሁ። ብልጽግና ለዛሬ ብቻ ሳይኾን ለትውልድ የሚሠራ፣ እስከ መቶ እና ሁለት መቶ ዓመታት በላይ አስቦ የሚሠራ፣ በኢትዮጵያ  ልክ ትልቅ አድርጎ የሚሠራ፣  አሁን ባለ ቴክኖሎጂ ልክ ጽድት አድርጎ የሚሠራ፣ ለሕዝቡ የገባውን ቃል ተግብሮ የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል። 

ባሕርዳር ከመቶ ዓመታት በላይ የምትሻገርበት፣ ውበት እና ክብርን የምትጎናጸፍበት ታላቁን ነገር አግኝታለች። በውበትም ደምቃለች።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት ቁርጠኛ መኾኑን መንግሥት አስታወቀ።
Next articleበማሽላ ዘር ብዜት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።