በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት ቁርጠኛ መኾኑን መንግሥት አስታወቀ።

31

ባሕር ዳር: ግንቦት 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በዘርፉ ከተሰማሩ ባለሃብቶች እና አምራች አርሶ አደሮች ጋር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርጓል። በዘርፉ የተሠሩ ሥራዎች፣ ያጋጠሙ ችግሮች፣ የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች እና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ውይይት ተድርጎባቸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የሞረትና ጅሩ ወረዳ አርሶ አደር ደመላሽ ይፍሩ በግል መሬታቸው ላይ በትራክተር በማልማት ስንዴ እና ጤፍ እስከ 200 ኩንታል እንደሚያመርቱ ተናግረዋል። የምርጥ ዘር ዓይነቶች ከሁለት ዓመት በኋላ ምርታማነታቸው ስለሚቀንስ ግብርና ምርምር የተሻሻለ የስንዴ ዝርያ እንዲያቀርብላቸው ጠይቀዋል። የአፈር ማዳበሪያም በበቂ መጠን እንዲቀርብ አሳስበዋል።

በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በአማራ ክልል 1 ሺህ 900 ባለሃብቶች በእርሻ ኢንቨስትመንት መሰማራታቸውን እና 280 ሺህ ሄክታር መሬት መውሰዳቸውን ገልጸዋል። የግሉ ዘርፍ ከግብርና ምርምር ጋር ትስስር ፈጥሮ ለውጥ እንዲያመጣ እንደሚጠበቅም ኀላፊው ገልጸዋል።

ሙያተኛን በአግባቡ አለመጠቀም፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን አለማሳደግ፣ የምርት ማሳደጊያ ፓኬጅን አለመጠቀም እና በአነስተኛ የእርሻ ማሳ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች የእውቀት ሽግግር እንዲያደርጉ አለመደገፍ የባለሃብቱ ውስንነቶች መኾናቸውን ዶክተር ድረስ ሳህሉ ተናግረዋል። እንቅፋቶች የበዙትን የክልሉን ግብርና ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ባለሃብቶች ከመንግሥት ከሚፈልጉት መካከል ሰላም ዋነኛው ጉዳይ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው ኅብረተሰቡ በተዛባ መንገድ በተደረገ ቅስቀሳ ወዳልኾነ አቅጣጫ ሄዶ እንደነበር ተናግረዋል። የክልሉ መንግሥትም ችግሩን ተረድቶ ከፌዴራል የጸጥታ ኃይል ጋር በመቀናጀት የኢንቨስትመንት ቦታዎችን ለመጠበቅ እና ሰላም ለማስከበር ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ ጉዳቱ መቀነሱን እና የሰላሙ ሁኔታም በሂደት እየተሻሻለ መኾኑን የጠቀሱት ዶክተር ድረስ ሕዝቡም በሂደት ከመንግሥት ጎን ኾኖ እያገዘ ስለኾነ በቅርቡ ችግሩ እንደሚፈታ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።

ኀላፊው በክልሉ መንግሥትም ኾነ ግብርና ቢሮ ዘርፉ በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ በቁርጠኝነት እየሠራን ነው ብለዋል። ከባለሃብቱ አልፈን አርሶ አደሮችን እያደራጀን ትራክተር እያቀረብን ነው። በባለሃብቱ ፍላጎት ልክ ማቅረብ ያልቻልነው በውጭ ምንዛሪ ችግር ምክንያት ነውም ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ እና የኢኖቬሽን ኤክስፖ ሊካሔድ ነው።
Next article“የመቶ ዓመታት መሻገሪያ፤ የአዲስ ውበት መደረቢያ”