
ባሕር ዳር: ግንቦት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የዓይን ሕክምና ክፍል አስተባባሪ ተስፋዓለም ጋሻው እንደገለጹት ሆስፒታሉ ከሰኔ 3 እስከ 7/2016 ዓ.ም የነፃ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና ሕክምና ይሰጣል።
የአይን ሞራ ግርዶሽ የብርሃን ማሳለፊያ ሌንስ ብርሃን የማሳለፍ አቅም ሲደክም የሚፈጠር ነው። በዋናነት በእድሜ መጨመር ምክንያት የሚከሰት ሲኾን በመመታት፣ በሰኳር በሽታ እና ተያያዥ በሽታዎች ምክንያት ሊከሰት እንደሚችል ነው አሥተባባሪው የገለጹት።
የዓይን ሞራ ግርዶሽ እይታን የሚቀነስ እና የዓይን ስውርነትን የሚያስከትል ቁጥር አንድ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል። ቀዶ ጥገና ደግሞ ዋነኛው መፍትሔው እንደኾነ አሥተባባሪው ገልጸዋል። ችግሩ እየጨመረ በመምጣቱ ሕክምናው ከመደበኛ ሕክምና ባለፈ በዘመቻ መንገድ እየተሰጠም ይገኛል።
ከዚህ በፊት በወረዳዎች የልየታ ሥራ ሲሠራ እንደነበር ያነሱት አሥተባባሪው በዚህ ዓመት በጸጥታ ችግር አገልግሎቱን በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለመሥጠት እንደተገደዱ ተናግረዋል።
አሥተባባሪው እንዳሉት ከግንቦት 17 እስከ 18/2016 ዓ.ም እና ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 1/2016 ዓ.ም የቅድመ ልየታ ሥራ ይካሄዳል። ከሰኔ 3 እስከ 7/2016 ዓ.ም ደግሞ ነፃ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና ሕክምና የሚሰጥ ይኾናል። በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የዓይን ሕክምና ክፍል አስተባባሪ የኾኑት ተስፋዓለም ጋሻው በተጠቀሰው ቀን ሆስፒታሉ በመገኘት ሕክምናውን ማግኘት እንደሚቻል ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!